





የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት በክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ላይ የሚመክር፣ የፀጥታ ግብረሃይል መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
በክልሉ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም በመገንባት የዜጎችን ሠላማዊ እንቅስቃሴ ለማረጋገጥ መጠነ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውንና በዚህም አዎንታዊ ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በክልሉ በአርብቶአደር አከባቢዎች አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የውስጥ የእርስበርስ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በመሠረታዊ ችግሮች ዙሪያ ከማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት መቋጫ ማበጀት እንደሚገባም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያሳሰቡት።
በክልሉ የማዕድን መውጫ አከባቢዎች አልፎ አልፎ ለሚከሰቱ ግጭቶች መንስኤዎችና አባባሽ ምክንያቶች በመለየት በጠንካራ የህግ ማስከበር ሥራ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ይገባል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በየደረጃው የፀጥታ መዋቅር የመፈጸም አቅም በማሳደግ፣ የሚስተዋሉ የፀጥታ ስጋቶችን በመለየት ቀድሞ የማምከን እና ወንጀሎች ተፈጽሞ ስገኝም የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ክልሉ ድንበር በሚጋራባቸው ቀጠናዎች የሚስተዋሉ ህገወጥ ንግድና የፀጥታ ስጋቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ በውይይት መፍታት የቅድሚያ አማራጭ መኾን እንዳለበት በማስገንዘብ የከፉ ችግሮች ስከሰቱ በፌዴራል መንግሥት ጠልቃ-ገብነት መፍታት ይገባል ብለዋል።
ህገወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም የጦር መሳሪያ ዝውውርን በቅንጅት መከላከል እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የፀጥታ ሀይል መልሶ ማደራጀትና የመረጃ ጥራት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
ለፖለቲካ ፍላጎት ማስፈፀሚያ፤ በህዝቦች መካከል መጠራጠር ለመፈጠር እንዲሁም ልማት ሠላምን ለማደናቀፍ የሚደረጉ የሀሰት ማንነትን ማዕከል ያደረገ የማህበራዊ የሚዲያ ዘመቻዎችን በህግ አግባብ መቆጣጠር እንደሚገባ ነው የመድረኩ ተሳታፊዎች ያነሱት።
የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በበኩላቸው፥ በየደረጃው የሚገኘው የፀጥታ መዋቅር ለቀጣይ ተልዕኮ ራሱን በብቃት ማዘጋጀት እንዳለበት በማንሳት የፖለቲካ አመራር ቁርጠኝነት መታከል አለበት ብለዋል።
የውስጥ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት አቅም መፈጠር አለበት ያሉት የኢፌዲሪ መከላከያ ተወካይና የክልሉ ፀጥታ ግብረ ሀይል ሰብሳቢ ሜጀር ጀነራል ታደሰ አመሎ፥ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን በየአደረጃጀቱ ለህብረተሰቡ በሠላም ዕሴት ግንባታ ላይ ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ መፈጠር አስፈላጊ መኾኑን ጠቁመዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
