




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የ2018 ዓ.ም የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ዉጤታማ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸዉ ተገልጿል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማትና መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዉብሸት ዘነበ እንደገለጹት የማህበረተሰብ የተቀናጀ ተፋሰስ ስራዎች ትግበራ በትኩረትና ከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄ በተሳካ ሁነታ የሚከናወን እንዲሁም ልማትና ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት የሚያረጋግጥ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል ።
በባለፈው ዓመት በመደበኛ 2መቶ 29ሺህ 750 ሄክታር መሬት በተፋሰስ ልማት ማልማት መቻሉንም ተናግረዋል።
የዘንድሮ ዓመት በተቀናጀ የማህበረተሰብ ተፋሰስ ልማት ስራዎች በነባር እና አዲስ ተፋሰስ 272 ሺህ 250 ሄክታር እንደሚለማ ገልጸዉ ለተግባሩም 1,305,598 የማህበረተሰብ ክፍሎችን እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።
የተለያዩ ስነ -አካላዊ እና ስነ-ህይወታዊ ስራዎች በተፋሰስ ልማት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዉ 22,220 ሄክታር የተጎዳ መሬት ከሰዉ እና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ እና በማካለል እንደሚለማ አስታዉቀዋል ።
የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የድጅታል ፋይዳ ምዝገባ እና ለሎች ተግባራት ከተፋሰስ ስራ ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራም አቶ ዉብሸት ተናግረዋል።
የ2018 ዓመተ ምህረት የተፋሰስ ልማት ስራ ከጥር 20/2018 ዓመተ -ምህረት ጀምሮ ለተከታታይ 30 ቀናት እንድሁም ዕቅዱን ለማሳካት ለተጨማር 15 ቀናት በድምሩ ለ45 ቀናት በማከናወን መጋቢት 4 እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።
የስራዉ ዝርዝር ተግባራት በክልል፣በዞን፣በወረዳና በቀበሌ ደረጃ እየተሰራ መሆኑን አቶ ዉብሸት ተናግረዋል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
