በባለፉት ለዉጥ ዓመታት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ በሰጠው ትኩረትና በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በክልሉ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ፦ አቶ ተመስገን ከበደ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ የመጋቢት 24 ፍሬዎችን በማስመልከት በክልላችን ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢንቨስትመንት ዘርፍ በተመዘገቡ ውጤቶች ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል ።

የቢሮ ኃላፊው በመግለጫውቸው በሀገራችን መጋቢት 24 /2010 ዓ.ም ከመጣው ሀገራዊ ለውጥ እርምጃዎች አንፃር ከዚህ በፊት በዘርፉ የነበሩ የአሰራር ቅልጥፍናን፣ አዋጅና ደንቦችን በመሻሻሉና እንደሀገር ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱ ዘርፉን ለማነቃቃት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል ።

ክልሉ የለውጡ መንግስት ትሩፋት መሆኑን ያነሱት የቢሮ ኃላፊው ከምስረታው በፊት የነበሩ የተለያዩ አሳሪ አዋጆች ደንቦችንና ጎታች አሰራሮችን በክልሉ መንግስት በመፈታቱ በኢንቨስትመንት ዘርፍ በፍጥነት መሻሻል መምጣቱንና ዘርፉን መነቃቃት መቻሉ ገልጸዋል ።

በመሆኑም የክልሉ ፀጋዎችን በቅድሚያ በመለየት ከለውጡ በፊት ከነበረው ከግብርና መር ወደ ብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ በመሸጋገሩ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፍ የተለያዩ ኢንቨስትመንት በመሳብ ክልሉ ብሎም ሀገርቱ ከዘርፉ የሚመነጨውን ኢኮኖሚ እንዲያገኙ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወኑን ተናግሯል ።

በክልሉ ብዙ የኤክስፖርት ምርቶች ለማምረት ዕምቅ አቅም መኖሩን ያወሱት አቶ ተመስገን በቡና ብቻ ክልሉ ሲመሠረት 34 ሺ ቶን ምርት ከነበረበት 54 ሺ ቶን ማድረስ መቻሉን የኢንቨስትመንት ተጽዕኖ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል ።

ከመጋቢት 24/2010 ወዲህ የለውጡ መንግስት በሰጠው ትኩረት በክልሉ ኢንቨስትመንትን ከመሳብም ከዚህ በፊት አንድ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ለማግኘት ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ይፈጅ የነበረውን ደንቡን በማሻሻልና ቀልጣፋ አሰራርን በመዘርጋት በአጭር ጊዜ ለአልሚዎች በማስተላለፍ ችግሩ እንዲፈታ ተደርገዋል ብለዋል ።

በዚሁ መሠረት ባለፉት 27 ዓመታት በክልላችን በግብርና 275፣ በኢንዱስትሪ 312፣ በሰርቪሰ 68 በአጠቃላይ 655 ፕሮጀክቶች ከነበረበት ባለፉት አጭር የለውጥ ዓመታት ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ ብቻ ከክልል እስከ ቀበሌ በቅንጅት በተሰራውና በተዘረጋው ቀልጣፋ አሰራር በግብርና 256 ፕሮጀክቶች 239 ሺህ 000ሄ/ር መሬት ለአልሚዎች ከተላለፈው ከ50% በላይ መልማት መቻሉን የቢሮ ኃላፊው አክሏል ።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ በእሸት ቡና መፈልፈያ እና ደረቅ ቡና መቀሸሪያ 39 ፕሮጀክቶች ወደ ስራ በመግባቱ የቡና ምርት መጠንም ሆነ ጥራትን በማሳደግ በኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፍ 56 ፕሮጀክቶች መተላለፉን ጨምረው ገልጸዋል ።

በዘርፉ ከተመዘገበው ለውጥ አንጻር በግብርናው ከውጭ ኤክስፖርት ምርቶች በ2014 ዓ/ም 1.6 ሚለየን ዶላር ክልላችን አስተዋጽኦ ሲያበረክት ከነበረበት አሁን 3.9 ሚለየን ዶላር መድረሱን አቶ ተመስገን በመግለጫቸው አንስተዋል ።

ከኢንቨስትመንት መሬት በአዋጅ ቁጥር 24/1996 የወጣው የኢንቨስትመንት መሬት መጠቀሚያ የግብር ክፍያ ዝቅተኛ 39 ከፍተኛ 63 ብር በሄክታር በመሆኑ በዓመት 6.5 ሚለየን ብር ሲያገኝ ከነበረበት አሁን ተሻሽሎ ዝቅተኛ 300 ከፍተኛ 500 ብር በመሆኑ ከመሬት መጠቀሚያ ግብር ብቻ ክልሉ በዓመት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማገኘት መቻሉን ገልጸዋል ።

የኢንቨስትመንት ዓላማው የዋጋ ንረትና ኑሮ ውድነትን መግታት፣ ለስራ አጦች የስራ ዕድልን መፍጠር እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት በመሆኑ የተጀመረውን የግብርና ዘርፉን በማጠናከር ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ ለመሸጋገር በትኩረት እንደሚሰራ እንዲሁም በአገልግሎት በማዕድንና ቱሪዝም ዘርፍ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል ።

በያዝነው ዓመት ብቻ ከ30 በላይ ፕሮጀክቶች ፀድቆ ወደ ስራ መግባቱን በማንሳት ይህ መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ማሳያ መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል ።

የማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር በዚህ ዓመት ብቻ 138ኪ/ሜ መንገድ በኢንቨስትመንት ዘርፉ በተሠማሩ ባለሀብቶች መሠራቱን በመጥቀስ የማህበረሰቡን ችግር ዘላቂነት ለመፍታት በቀጣይ ከሌሎች ጋር በቅንጅትና በመናበብ እንደሚሰራ አንስተዋል ።

ለአልሚ ባለሀብቶች የመሠረተ ልማት ችግሮችን በመፍታት ምቹ ሁኔታውን ለመፍጠር መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው በመንግሥት አቅም ብቻ የማይፈቱ ችግሮች በባለሀብቶች እንዲፈቱ የማስተባበር ሚና እተወጣ እንደሆነ ተናግረዋል ።

መጨረሻም ከመጋቢት 24/2010 ዓ/ም ጀምሮ የለውጡ መንግስት ያመጣውን ዕድል በመጠቀም በክልሉ ባጠቃላይ በኢንቨስትመንት ዘርፍ በተለይ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የክልሉ መንግስት ተቀብሎ በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጁ በመሆኑ እንዲሣተፉ ጥሪውን አቀርበዋል ።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *