


የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከቤላሩስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ሪዤንኮፍ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት በቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፥ ቤላሩስ በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ለኢትዮጵያ ላደረገችው ድጋፍ በማመስገን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና በሌሎች ዘርፎች አበረታች ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን ጠቁመው፥ ከአጋር ሀገራት ጋር ለምታደርገው ትብብር በትኩረት እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡
ተወዳዳሪነትን በማጠናከር የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር በመሰረተ ልማት፣ በሰው ሃይል ግንባታና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዘርፎች የአጋር ሀገራት ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ማክሲም ሪዤንኮፍ በበኩላቸው፥ ቤላሩስ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራትና ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል፡፡
በተለይም በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በማዕድን፣ በንግድ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በተመረጡ ዘርፎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ቀጣይነት ያለው ውይይት ለማካሄድ መስማማታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል ሲል ኤፍኤም ሲ ዘግቧል፡፡
