ኢትዮጵያ እና ቤላሩስ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በሚያረጋግጡ መስኮች ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ

Spread the love

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የቤላሩስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ሪዜንኮቭን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሚኒስትሮቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ እ.አ.አ በኦክቶበር ወር 2024 በሩሲያ ካዛን ከተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ጎን ለጎን ያደረጉትን የሁለትዮሽ ውይይት አንስተዋል።

ውይይቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

ጌዲዮን (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከቤላሩስ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትስስር ለማጠናከር እና የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የትብብር አማራጮችን ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ የቤላሩስ ባለሀብቶች በግብርና፣ግብርና ማቀነባበሪያ፣ ማዕድን፣ በተፈጥሮ ጋዝ እና ነዳጅ፣ግንባታ፣ንግድ እና ቱሪዝምን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ሊሰማሩባቸው የሚችሉባቸው በርካታ እድሎች እንዳሉ አንስተዋል።

የቤላሩስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ሪዜንኮቭ፥ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቷን ለማጠናከር እና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡ የትብብር አማራጮችን ለመለየት ዝግጁ ናት ብለዋል።

ሁለቱ ወገኖች ሀገራቱ በባለብዝሃ ወገን የትብብር አማራጭ መስራት በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመረጃው አመልክቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *