



ነባር ቅርሶችን በማልማት ለትውልድ ለማስተላለፍ ከተሠሩ ሥራዎች ወካከል አንዱ የጀጎል ግንብ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።
በሚኒስትር ዴኤታው የተመራው የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ቡድን በሐረር ከተማ የመስክ ምልከታ እያደረገ ይገኛል።
አቶ ተስፋሁን በዚሁ ወቅት እነደተናገሩት መንግሥት ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፍ እንዱ ሲሆን ይህን ትኩረት ተከትሎ በሀገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የነበሩ ቅርሶችን በማደስ እና አዳዲስ መዳረሻዎችን በማልማት ረገድ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል።
ነባር ቅርሶችን በማልማት ለትውልድ ለማስተላለፍ ከተሠሩ ሥራዎች ወካከል የጀጎል ቅርስ አንዱ እንደሆነም ነው የገለጹት።
የሐረር ጆጎል ግንብ እድሳት የሚያሳየው ከተሞቻችን ሲታደሱ እና ዘመናዊነት ሲጨምሩ የነበር ታሪካቸን ቆርጦ መጣል ወይም አፍርሶ መነሣት እንደማይጠበቅባቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።
የጀጎል ግንብ ከሌላው የሚለየው ኅያው ቅርስ /living heritage/ መሆኑ ነው ያሉት አቶ ተስፋሁን፣ በውስጡ ሕይወት ያለበት የሰዎች መኖርያ መሆኑ እንደሆነ እና ይህንን ኅያው የሆነ ቅርስ ኅያውነቱን በጠበቀ መልኩ ለማደስ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸው ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የክልሉ መንግሥት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እና በልዩ ትኩረት ለሥራው የሚያስፈልገውን ወጪ የተለያዩ የክልሉ ተቋማት ሥራውን ተከፍፍለው በመተባበር በውስጥ አቅም መሥራት መቻላቸው ከፍተኛ ውጤት ተግኝቷል ብለዋል።
“ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለሃምሳ ሰው ጌጥ ነው” እንዲሉ አበው፣ በአንድ ዓላማ ላይ በትብብር መንፈስ ከተንቀሳቀስን የማናሳካው እንደማይኖር ማሳያ ነው ሲሉም አክለዋል።
በሀገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ቅርሶች ታሪካዊነታቸውን በጠበቀ እና በሚያጎላ መልኩ በጥንቃቄ እና በዘርፉ ባለሞያዎች እየታደሱ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
በሐረር ጀጎል ግንብ ቅርስ የታየውን ታሪክን ጠብቆ የማቆየት ሥራ በሀገራችን በሌሎች አከባቢዎችም በስፋት እየተሠራበት እንደሆነ አስታውሰው፣ ለዚህም የጎንደር ፋሲለደስ እና የጅማ አባጅፋር ቤተመንግሥት እድሳት እንደ ማሳያ ማንሳት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ከተሞቻችን ታሪካዊነታቸን እና ዘመናዊነታቸውን አጣምረው ፈክተው እንዲቆዩ በማድረግ ረገድ ያለፉት ሰባት ዓመታት እምርታዊ ለውጥ ያመጡ ስለመሆናቸው መግለጻቸውንም ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
