የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መምህራን ማህበር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የሚያግዙ ጥናታዊ ጽህፎች እንዲቀርቡ አደረገ።

Spread the love

በማህበሩ የተዘጋጀ 3ኛ ዙር ክልላዊ የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ለትውልድ አሻራ እያሳረፉ ከሚገኙ አካላት መካከል መምህራን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ብለዋል።

ዛሬ ለተደረሰበት የዕድገት ደረጃ የመምህራን ሚና የማይተካ ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ መምህራን ማህበር ለተከታታይ 3 ዓመታት የትምህርት ጥራት ኮንፈረንሶችን እያካሄደ መቆየቱን አስታውሰው ፤ ኮንፈረንሱ በትምህርት ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ በጋራ መስራት ወሳኝ ነው ብለዋለ፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከማህበሩ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕረዝደንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ የክልሉ መምህራን ማህበር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በተደራጀ በአጭር ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ ጥናታዊ ጽህፎች እንዲቀርቡ ጥረት ማድረጉ የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ሪፎርም ውስጥ መግባቱን የተናገሩት ፕረዝዳንቱ፣ አጀንዳ በመቅረጽ በየዓመቱ ችግር ፈቺ የሆኑ ውይይቶችን ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡

በዚህም የማህበሩን ውስጣዊ ጥንካሬ በሁለንተናዊ መልኩ ማረጋገጥ እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት፡፡

የክልሉ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አካሉ አለማየሁ በበኩላቸው ፤ የክልሉ መምህራን ማህበር የትምህርት ጥራት መረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የመምህራንን መብትና ጥቅማ-ጥቅም ከማረጋገጥ አኳያም ከተለያዩ ባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አካሉ ፤ የማህበሩን የሥራ እንቅስቃሴ የሚያስቃኝ የመጽሔት ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል፡፡

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ-ልማት ለማሻሻል በተደረገ ጥረት የማህበሩ አባላት ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የሚስተዋለውን የትምህርት ጥራት መጓደል ለመቅረፍ ማህበሩ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ምሁራን የተዘጋጁ ጥናቶችን በማቅረብ ጉድለቶች እንዲታዩ የማድረግ ሥራ መሥራትን አብራርተዋል፡፡

በዚህም ጥናቱን መሠረት በማድረግ የተቀመጠውን ምክረ-ሃሳብ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ የካፋ ዞን መምህራን ማህበር በዞን ደረጃ ስልጠና በመስጠት ለትምህርት ቤቶች እንዲወርድ ማድረግ መቻሉን የቦንጋ ኤፍ ኤም ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *