






በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ክልል አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ምዘና ውድድር ተጠናቀቀ፡፡
በውድድሩ የመዝጊያ ስነስርዓት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ሃላፊ ተወካይና የስፖርት ተሳታፊነትና ውድድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በየነ ቴቃ ፕሮጀክቱ ለአራት ዓመታት ተቋርጦ በአዲስ ፎርማት ዳግም መጀመሩን ተናግረዋል።
ዓላማውም ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ ስፖርትን ለማሳደግ እንደሆነ አብራርተዋል ።
እንደ ክልል የፕሮጀክቱን ምዘና በአስራ ዘጠኝ ዘርፎች ለማካሄድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም የዞኖች ተሳትፎ በማነሱ ምክንያት የታሰበውን ያህል አለመሆኑን አስረድተዋል።
የክልሉ ድጋፍና ክትትል በዘርፉ በቂ ያለመሆኑም በሌላ በኩል ለዚሁ አስተዋፅኦ ያበረከተ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በዉድድሩ በክልሉ ካሉ ስድስት ዞኖች መካከል ካፋና እና ምዕራብ ኦሞ ያልተሳተፉ ሲሆን ሌሎቹ በእግር ኳስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስና በአትሌቲክስ በሁለቱ ፃታዎች የተሳተፉበት ስለመሆናቸውም ገልፀዋል።
በሥነ ስርዓቱ ላይ ያነጋገርናቸው ስፓርተኞች፣ አሰልጣኞችና የስፓርት ቤተሰቦችም ተቋርጦ የነበረዉ ፕሮጀክት መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ገልፀዉ ከሚመለከታቸው አካላት ለስፓርቱ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ግን እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል ።
በምዘናዉ በጠረጴዛ ቴኒስ በሁለቱም ፃታዎች የኮንታ ዞን፣ በእግር ኳስ በወንዶች የዳውሮ ዞን እና በአትሌቲክስ የሸካ ዞን የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል ።
ውድድሩ እንዲሳካ ጉልህ ሚና ለተጫወቱት ግለሰቦችና ተቋማትን የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል ሲል ደሬቴድ ዋካ ቅርንጫፍ ዘግቧል።
