ቡና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተጨባጭ ዋልታነቱን እያስመሰከረ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

Spread the love

ቡና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተጨባጭ ዋልታነቱን እያስመሰከረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቡና ምርት ላይ ለተሰማሩ ውጤታማ አርሶ አደሮች፣ አልሚዎች፣ ቡና ላኪ ማኀበራት እና ባለሐብቶች ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥተዋል፡፡

ሀገራዊ የቡና ኤግዚቢሽን እና የዕውቅና መድረክ በሳይንስ ሙዝየም ተከናውኗል፡፡

በመድረኩ ላይ 64 የቡና ላኪዎች፣ አምራቾች እና የኢንቨስትመንት ተቋማት የዋንጫ እና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓመት 1 ሚሊየን ቶን ቡና ማምረት መቻሏን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት 3 መቶ ሺህ ቶን የሚጠጋ ቡና ለዓለም ገበያ ቀርቦ ከ1.4 ቢሊየን ዶላር በላይ መገኘቱን ጠቁመው፤ “ይህም ቡና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተጨባጭ ዋልታነቱን የሚያስመሰክር ነው” ብለዋል፡፡

በቡና ምርት ከብራዚል እና ቬትናም ቀጥላ በዓለም 3ኛ የሆነችውን ኢትዮጵያን ከቬትናም ጋር እኩል ለማድረግ ምርት ማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አበክረዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሀገሪቱ የስፔሻሊቲ ቡናን 60 በመቶ ማድረስ መቻሏን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ 1 ኪሎ ግራም ቡናን በ103 ሺህ ብር መሸጥ መቻሏንም አስታውቀዋል፡፡

በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የቡና ምርትን ለማሳደግ እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ እንደሚሰራም አመላክተዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *