

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ ከምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም /FSRP/ ጋር በመተባበር የ2017 ዓ.ም የበጋ መስኖ ልማት ላይ ለዞንና ወረዳ ባለሙያዎች የክህሎት ስልጠና በሚዛን አማን ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
ስልጠናው የበጋ መስኖ ሰብሎች አመራረት፣የመስኖ ውሃ አጠቃቀም እንዲሁም በGPS እና GIS አጠቃቀም የመረጃ አመዘጋገብ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ በስልጠናው ማስጀመሪያ በክልሉ በበጋ መስኖ ልማት በአንደኛ እና ሁለተኛ ዙር ከ95 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዬ ሰብል ለመሸፈን ታቅደው እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በ2017 ዓ.ም በበጋ መስኖ ልማት ከ12 ሺ ሄክታር በላይ ማሳ በስንዴ ልማት እንዲሁም 83 ሺህ ሄክታር ማሳ በአትክልትና ስራስር ሰብሎች ይሸፈናሉ ነው ያሉት።
በምርት ዓመቱ በበጋ ስንዴ ልማት እንዲሁም በአትክልትና በስራስር ሰብሎች በአጠቃላይ ከ95 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ከሚሸፈነው ውስጥ 19.2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በክልሉ በ2014 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በዚህም የማሳ ሽፋኑና ምርትና ምርታማነቱ በየዓመቱ ዕድገት እያሳዬ መምጣቱም ተገልጿል።
አቶ አሸናፊ ክንፉ በማከልም ስልጠኞች ከስልጠናው የጨበጡትን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም የምርት ዓመቱ ዕቅድ እንዲሳካ የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ግዴታ ጭምር እንዲወጡም አሳስበዋል።
ለሶስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ከ250 በላይ የሚሆኑ የግብርና ባለሙያዎችም እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በፍቅር ከበደ
