የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ለህ/ሰቡ የጤና አገልግሎት በፍትሀዊነት ተደራሽ ለማድረግ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ።

Spread the love

የክልሉ የህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን (ማአጤመ) ቦርድ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የመዋጮ ክፍያ ምደባ ለማሻሻል በቀረበው መመሪያ አተገባበር ላይ ውይይት በታርጫ ከተማ አድርጓል።

የቦርዱ ሰብሳቢ እና በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ የማህበረሰብ አቀፍ መድን አገልግሎት ለህብረሰቡ የጤና አገልግሎት በፍትሀዊነት ተደራሽ ለማድረግ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አቅም ባገናዘበ ልክ ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ በመሆኑ ሁሉም የክልሉ አመራሮች ክልል አቀፍ ውይይት ከተደረገ በኋላ ለተፈጻሚነት ኃላፊነት ወስደው መስራት የሚችሉበት አግባብ ይፈጠራል ብለዋል።

የአባልነት ምልመላ በሚፈጸምበት ጊዜ በጥብቅ ዲስፒሊን እንደሚመራ ገልጸው በቀጣይ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የውስጥ አሰራር ግልጽ ሆኖ የሚመራበት ስርዓት በሚፈጠርበት አግባብ ላይ ይሰራል ብለዋል።

በአተገባበር መመሪያ ላይ የማአጤመ የቦርድ አባላት ውይይት ያደረጉበት ሰነድ ለሚመለከተው አካል ቀርቦና ተገምግሞ ከጸደቀ በኋላ በአጭር ጊዜ በስራ ላይ ይውላል ብለዋል አቶ አልማው ።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በማዐጤመ አተገባበር መመሪያ ላይ ህብረተሰቡ ግልጸኝነት እንዲፈጥር በተዋረድ ለሚገኙ አስተዳደራዊ እርከን ለዞን እና ወረዳ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ መስጫ መድረክ መዘጋጀቱን ገልጸዋል ።

በዞን ጤና መምሪያዎች የማዐጤመ ጉዳዮች የሚያስፈጽሙ ባለሙያዎች ዞኖች ባላቸው የስራ ጫና እና ስፋት ልክ ባለሙያ እንዲሟላ ከስቪል ሰርቪስ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የማዐጤመ አፈጻጸም ስኬታማ እንዲሆን በግልና በጋራ ግንባር ቀደም ሚና ለሚጫወቱ አካላት የማበረታቻ ሽልማት ስርዓት እንደተዘጋጀም ገልጸዋል።

በአዲስ መንገድ የተከለሰው የማአጤመ መመሪያ በ2017 በጀት አመት የሚተገበር በመሆኑ የገለጹት ሀላፊው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለስኬቱ የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት ብለዋል።

መመሪያውን ለቦርዱ አባላት ያቀረቡት የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሚዛን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ ስኪያጅ አቶ ታከለ ታደሰ ከዚህ በፊት የማህበረሰብ ጤና መድን መዋጮ በፌደራል ደረጃ የተሰራውን ጥናት መነሻ በማድረግና ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች በየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ሲወስኑ የነበረ ቢሆንም አወሳሰኑ በዋናነት የከተማና የገጠር ነዋሪዎችን ታሳቢ ሳያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ የሁሉም ክልሎች የማአጤመ የአተገባበር ስርዓት ወጥ ሆኖ የሚመራበት አግባብ መፈጠሩን ገልጸው የደንበኞች መዋጮ አከፋፈል በዝቅተኛ፣ በመካከለኛ እና በከፍተኛ የክፍያ ደረጃ ምደባ መስተካከሉን ተናግረዋል።

በአዲስ መልክ በቀረበዉ የአፈጻጸም መመሪያ መሰረት ተፈጻሚ እንዲሆን አስቀድሞ ዝርዝር ዕቅድና ትግበራ ተዘጋጅቶ በየደረጃው ለሚገኙ የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደሮች የግንዛቤ መስጫ መድረክ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የቦር አባላት በቀረበው መመሪያ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ካለው ጠቀሜታ አንጻር ለተፈጻሚነት ሁሉም አካል ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *