



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ፋይናንስ ቢሮ በመንግሥት ግዥ ንብረት ባለስልጣን ለወረዳ የግዥ ባለሙያዎች በካልም ፕሮግራም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በሚዛን አማን ከተማ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
በስልጠናው የክልሉ ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ኦዲትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ታምራት ወርቁ ስልጠናው ግልጽና አሳታፊ የግዥ ስርዓትን በማስፈን ለግዥ የሚመደበው ውስን የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ ለማዋል እንደሚረዳም ገልጸዋል።
አስፈላጊ የግዥ ሂደት እንዲኖርና የንብረት አያያዝ ሥርዓት እንዲስተካከል የስልጠናው ፋይዳ የጎላ ከመሆኑም ባሻገር ሀብትን በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር የባለሙያዎችን የክህሎት ውስንነትን የሚቀርፍ ነው ብለዋል።
ስልጠናውን ከተሳተፉት መካከል አቶ ባንታየው እሸቱ፣ ወ/ሪት አይናለም ደምሴ እና አቶ ዋስሁን ለገሰ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው በግዥ አስተዳደር እና በንብረት አያያዝ እንዲሁም የተፈቀዱ የግዥ ሂደቶችን በመከተል ግዥ ለማከናወን ፋይዳው የጎላ ከመሆኑም ባሻገር ለቀጣይ ሥራቸው በቂ እውቀትን እንዲጨብጡ ያስቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የግዥ ስርዓቱ ግልጽ፣አሳታፊና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሆኖ እንዲቀጥል ስልጠናው ቀጣይነት እንዲኖረውና ለሚመለከታቸው አካላትም ጭምር መሰጠት ይገባል ብለዋል በአስተያየታቸው።
ስልጠናው በመንግስት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ ፤የመንግስት ግዥ ትርጉም፤በግዥ ዓይነቶች፤ግዥ አላማና መርሆች፤ዋና ዋና ተግባርና ኃላፊነቶች፤የግዥ ዕቅድና በተፈቀዱ ግዥ ዘዴዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
በፍቅር ከበደ
