



ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የሽግግር ፍትህ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ድጋፍ እንደምታደርግ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ገለጹ።
አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ ጉብኝት አድርገዋል።
አምባሳደሩ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ለአምባሳደሩ በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን መሰረት አድርጎ ልዩ ችሎት የማቋቋም ሂደትን በተመለከተ እንዲሁም በሌሎች የሪፎርም ሥራዎች ዙሪያ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ትግበራ ላይ ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸውን ሚና ለመተግበር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትብብር ማድረግ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም ውይይት ተደርጓል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ፍርድ ቤቱ በሽግግር ፍትህ ፖሊሲው አማካኝነት ነፃ እና ገለልተኛ ልዩ ችሎት ለማቋቋም የህግ ማርቀቅ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ችሎቱን የማደራጀት ተግባር የፍርድ ቤቱ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው፤ ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመላኩ በፊት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የህዝብ ውይይት ለማድረግ በዝግጅት እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ፈረንሳይ የሽግግር ፍትህ ትግበራ ሂደት ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸውን የፍርድ ቤቱ መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
