



የኢቢሲ ወደ ይዘት ጉዞ አካል የሆነው አዲሱ የታርጫ የኢቢሲ ስቱዲዮን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እና የኢቢስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በተገኙበት ተመርቆ ስራ ጀምረዋል ።
በምረቃ ስነስርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ክልሉ ብዙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች እንዲሁም ማህበራዊ ድልብ ዕሴት ባለቤት መሆኑን በመጥቀስ ይህን በይፋ ለማውጣት የክልሉን ዕድገት ለመገንባትና ለማፋጠን ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
ክልሉ ብዙ የብሔረሰቦች መገኛ በመሆኑ ገዥ ትርክትን በመገንባትና የባህል፣ ታርክና ዕሴቶችን አጉልቶ ከማሳየትም ባሻገር በልማት የተረሱ አካባቢዎችን ለልማት ለማነሳሳት እንደሚጠቅምም ተናግረዋል።
የተመረቀው የሚዲያ ተቋም ህዝብንና መንግስትን በማስተሳሰር ድልድይ ሆኖ ከማገልገሉም ባሻገር ራሳችንን መልሰን የሚናይበት መስተዋት ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳደሩ፡
የተዛቡና የተሳሳቱ መረጃዎች እንደ አሸን በፈሉበት በድህረ እውነት ዘመን ትክክለኛና ተአማንነት ያለውን መረጃ ለህዝቡ በቅርበት በማድረስ ሚናውን እንደሚጫወት አንስተዋል።
ስራውን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቁ በሀገራችን የትኛውንም ፕሮጀክት መስራትና ማሳካት እንደምንችል አቅም መኖሩን ማሳያ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል ።
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ኢቢሲ ኢትዮጵያን በመገንባትና በሀገረ መንግስት ግንባታ የላቀ አሻራን ከማሳረፍ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ያለው ዕድሜ ጠገብ ተቋም መሆኑን አንስተዋል።
ባለፉት 7 ዓመታት ጠንካራ ሪፎርምና ጠንካራ ተቋም ያስፈልጋል ተብሎ መንግስት ከሰራቸው አንዱ ኢቢሲ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ቢቂላ ውጤቱም በሀገራች ባለፉት ዓመታት ወንድማማችነትና አንድነት የተጠናከረበት በሌላ መንገድ ቂም፣ ጥላቻና መሠል ተግባራት ከገበያ እየወጡ የመጡበት መሆኑን ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ቀኝ እጅ የሆነው ሚዲያን ወደ ህዝብ በመቅረቡ የባለድርሻ አካላት በትብብርና ቅንጅት መጠቀም እንደሚገባው በመጥቀስ የሚያዳመጡት ብቻ ሳይሆን የሚናገሩበት እንዲሆንም አሳስበዋል ።
የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ኢቢሲ ረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብን በተለያዩ ይዘቶችና ቋንቋዎች በማገልገል ላይ የሚገኝና በሪፎርም ውስጥ ወደ ህዝብ ወርዶ እያገለገለ ያለ ተቋም መሆኑን አንስተዋል።
የሪፎርሙ ዓላማውም ተቋሙን በአደረጃጀትና በአሰራር እንዲሁም በሰው ኃይል በማዘመን የፓን አፍሪካ ሚዲያ ለመሆንና ወደ ህዝብ ወርዶ ማገልገል መሆኑን በማንሳት ዛሬ የተመረቀው ስቱዲዮ የዚህ ውጤት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል ።
የሰብአዊ መብት ጥበቃና የዴሞክራሲ ግንባታ ስርዓት ግንባታ ያለ ሚዲያ ዕውን አይሆንም ያሉት በኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አዝመራው አንደሞ ናቸው።
የተመረቀው የሀገር አቀፍ ሚዲያ የክልሉ ህዝቦችን በማስተሳሰር ህብረብሔራዊነትንና አንድነትን ለማጠናከር እንደሚጠቅም በመግለጽ ለሚዲያና ለህዝብ የሚጠቅሙ ህጎችን በማውጣትና ተፈጻሚነትን በመከታተል ረገድ ቋሚ ኮሚቴው አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አደሎ የሰብዓዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ በማስተማርና ግንዛቤ በማስጨበጥ በቅንጅት እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል ።
በመሆኑም ሚዲያን በቴክኖሎጂ ከማዘመንና የጋዜጠኞች ስነ ምግባር ላይ በቀጣይ በቅንጅትና በትኩረት ተጠናክሮ እንደሚሰራአቶ ብርሃኑ ተናግረዋል ።
የእንኳን ደህና መጣችሁ ያሉት የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ የስቱዲዮ መገንባት አካባቢውን የሚዳሰስና የማይዳሰሱ ቅርስና ዕሴቶችን ከማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ተናግርዋል ።
ሚዲያው የህዝብ ድምፅ ከመሆኑም በላይ አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ኢትዮጵያዊነት ለማቀንቀን አጋዥ መሆኑን በማንሳት ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱት አካላት ምስጋና አቀርበዋል።
ከስቱዲዮ ምርቃ ጎን በአንግዶቹ በዳውሮ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስና የምርምር ማዕከል ግቢ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ተካሂደዋል፤ ለስኬታማነቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱት አካላትም የዕውቅና ሽልማት ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል ።
በጌታሁን ግርማ
