በቀጣናው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረጉ ጥረቶች ድጋፍ ይደረጋል -ኢጋድ

Spread the love

በቀጣናው የምግብ ዋስትናን፣ የግብርና ምርታማነት ለማረጋገጥ ለሚደረጉ ጥረቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አስታወቀ።

የኢጋድ የመስኖ ስትራቴጂ ጥናት ማረጋገጫ ወርክሾፕ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ሲሆን በመድረኩ የቀጣናው አባል ሀገራት ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በኢጋድ የኢኮኖሚ ትብብር እና ቀጣናዊ ትስስር ዳይሬክተር ሞሄለዲን ኤልቶሀሚ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ቀጣናው ተደጋጋሚ ድርቅንና የውሃ አቅርቦት ችግሮችን እየተጋፈጠ ነው።

የኢጋድ አባል ሀገራት የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር ለመስኖ ልማትና ለውሃ ሀብት አያያዝ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የመስኖ ስትራቴጂው በቀጣናው የመስኖ እና የግብርና ልማት አቅምን ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለአካባቢ መራቆት መፍትሄ ለመስጠት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣናው ለእርሻ ምቹ የሆነ መሬት መኖሩን ተከትሎ የግብርና ምርታማነትን በመስኖ በመደገፍ ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥናት እና ዲዛይን መሪ ስራ አስፈጻሚ ያሬድ ሙላት በበኩላቸው አባል ሀገራቱ ተደጋጋሚ ድርቅ እና የውሃ አቅርቦትና ስርጭት ችግር በሚያስከትሉት ጉዳት እየተፈተኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በግብርናው ዘርፍ መስኖን ማስፋፋት፣ የግብርና ምርታማነትን ማሻሻል፣ የገጠር ነዋሪዎችን ዘላቂ ኑሮ ማረጋገጥ፣ ድህነትን ለመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዋነኛው መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የመስኖ ልማት እና የውሃ አያያዝ ማዕቀፍ በመቅረጽ እና መርሆዎቹን በመተግበር ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል።

ማዕቀፉ አህጉራዊ ዕቅድ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች በአብዛኛው ከዓላማዎቹ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንግሥት የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የዝናብ ውሃ አሰባሰብ እና የውሃ ተፋሰስ አያያዝ ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ፣ መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ እንደምትገኝ አስታውቀው፤ ያሉትን እቅዶች ለማዘመን እና አፈጻጸማቸውን ለማሻሻል የሚረዱ ጥረቶች መቀጠላቸውን አንስተዋል።

በመስኖ የሚለማ የስንዴና የሩዝ ምርት እንዲሁም አረንጓዴ አሻራ ተፅዕኖ የፈጠሩ ሀገራዊ የለውጥ ኢኒሼቲቮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የስትራቴጂው ሚና ታላቅና ያልተነካ ሀብት ያላት አፍሪካ፣ የበለጠ ምርታማና ተቋቋሚ የሆነ የወደፊት ጊዜን ለማረጋገጥ የሚያስችላት መሆኑን ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *