ክልሉ በኦሎምፒክ ውድድሩ 6 ሜዳሊያዎችን ማግኘት መቻሉ ተገለጸ።

Spread the love

በአዲስ አበባ ስካሄድ የቆየው 2ኛው የታዳጊ ወጣቶች አገር አቀፍ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ተጠናቋል።

ላለፉት ስምንት ቀናት በአዲስ አበባ ስካሄድ በቆየው 2ኛው የታዳጊ ወጣቶች አገር አቀፍ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 6 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ‎መቻሉን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገልጿል።

የቢሮ ምክትል ሀላፊና የስፖርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ዳዊት ደስታ ለሚዲያችን በሰጡት መግለጫ ወድድሩ ከሜዳሊያ በዘለለ ልምድ የተገኘበት እንደሆነም አብራርተዋል።

አቶ ዳዊት አክለውም በቀጣይ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ ለተተኪው ወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በትምህርት ቤቶች፣ በየአካባቢያቸውና በቀበሌ ደረጃ ህብረተሰቡን በማስተባበር ማጠናከር እንደሚገባም አስረድተዋል።

የስፖርት ዘርፍ ውጤታማነት በመንግስት በጀት ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም ያሉት ምክትል ሀላፊው በተለይ የህብረተሰብ ተሳትፎ በማሳደግ ስፖርት ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ይሰራልም ብለዋል።

በውድድሩ ቀጥሎ ለሚካሄደው ለአፍሪካ ኦሎምፒክ ጨዋታ ሀገራችንን ወኪለው ከሚሳተፉ ወጣቶች መካከል ከክልሉ በጊዜያዊ ምልመላ ውስጥ የተካተቱ መኖሩን የገለፁ አቶ ዳዊት የዕድሜና መሠል ነገሮች ከታዩ በኃላ የተመለመሉ ስፖርተኞች በቀጥታ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

በውድድሩ የክልሉ ስፖርት ልዑካን 1 ወርቅ ሜዳልያ፣ 1 ብር ሜዳልያ፣ 4 ነሐስ ሜዳልያዎች በድምሩ 6 ሜዳልያዎችን ማስመዝገብ ችሏል።

ቢሮው በተለያዩ ዘርፎች ውጤት ላስመዘገቡና ለተሳተፉ ስፖርተኞች የእውቅናና የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት መስጠቱንም አቶ ዳዊት አስረድተዋል።

‎3ኛውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ትግራይ ክልል ለማስተናገድ እድሉን መወሰዱ ታውቋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *