




የኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት ከክልል እና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ፣ ፍትህ ቢሮ፣ ከፋይናንስ ቢሮ እና ከዋና ኦዲት ቢሮ ከተውጣጡ ኃላፊዎች እና ጥሪ ከተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር፣ የጤና መድኅንን ለማስቀጠል እና የፋይናንስ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ በሚተገበሩ ተግባራት ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ እንደገለጹት፣ የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድኅን ለማስቀጠል የፋይናንስ ዘላቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የፋይናንስ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ደግሞ ከፍ ያለ ቋት መመስረት ፣ አባላት በአቅማቸው መጠን ማዋጣት እና የተሰበሰበው ገንዘብ በአግባቡ የኦዲት ስራ እየተሰራና ለጤና አገልግሎት ብቻ ማዋል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ይህንንም ለማድረግ በየደረጃው ያለው የአስተዳደር እርከን የፌደራል፣ የክልል እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እና በመግባባት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት የአባላትና ሀብት አሰባሰብ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ጉደታ አበበ በበኩላቸው፣ በ2014 ዓ.ም በ13 ወረዳዎች የተጀመረው የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድኅን ተደራሽነት፣ እስከ የካቲት 28/በ2017 ዓ.ም 1213 ወረዳዎች መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
አሁን የደረሰውን ውጤት ዘላቂ ለማድረግ እና በሁሉም አካባቢ ተመሳሳይ ውጤት እንዲመጣ የሚመለከተው አካል በቂ ስራ መስራት አለበት ብለዋል፡፡ በተለይ አባላት የሚያዋጡትን ገንዘብ፣ መክፈል ለማይችሉ የሚደጎም የክልሎች የተናጠል ድጎማ እና የፌደራል ጥቅል ድጎማ በአግባቡ ተሰብስቦ በህጋዊ መንገድ በኦዲት ተረጋግጦ ለተጠቃሚዎች የህክምና አገልግሎት ብቻ ማዋል እንዳለበት አቶ ጉደታ አሳስበዋል፡፡
አቶ ሙሉቀን አስማማው በኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት አማካሪ በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድኅን ያለውን ተጽእኖ ማየት፣ ማጭበርበርን ማስወገድ ፣ ሀገራዊ የጤና ሽፋንን ማሰብ፣ አባላት በአቅማቸው መሰረት እንዲያዋጡ ማድረግ እና ከፍ ያለ ቋት እንዲመሰረት እያሰቡ መስራት እንደሚገባ ባቀረቡት ገለጻ አመላክተዋል፡፡
ተሳታፊዎች በበኩላቸው እስካሁን እየተሰራ ያለው የማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድኅን ስራ ውጤታማ በመሆኑ ጥንካሬዎቻችን ለማስቀጠል እና ጉድለቶችን እየለዩና መፍትሔ እያስቀመጡ የተሻለ ስራ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድኅን ዜጎች ካልታሰበ የወጪ ስጋት የሚታደጉበት ፣ እናቶች ህጻናት ታክመው የሚድኑበት እና የህክምና ተደራሽነትን የምናረጋግጥበት በመሆኑ ትኩረት የሚሰጠው እና የጤና ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
መሻሻል በሚያስፈልጉ ጉዳዮች እንደ የመድኃኒት አቅርቦትን ማሻሻል እና አሰራርን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዲጂታላይዝድ ማድረግ የበለጠ አሰራሩን ግልጽና ተአማኒ ስለሚያደርገው ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት ሲሉ ተሳታፊዎቹ አሳስበዋል፡፡
