በቦንጋ ከተማ የመንገድ ዳር መብራት ሽቦ የሰረቀ ተከሳሽ እና የተሰረቀ ሽቦዎችን ከሌባ የገዛ አንድ ግለሰብ በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸዉን በካፋ ዞን ፍትህ መምሪያ አስታወቀ

Spread the love

ወንጀሉ የተፈጸመው በካፋ ዞን በቦንጋ ከተማ አስተዳደር ጥር 7 ቀን 2016 ዓ.ም ከንጋቱ 12:00 ሰዓት በዩንቨርስቲ ቀጠና አበቺ መንደር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን ወንጀሉን የፈፀሙት ታረቀኝ ቆጭቶና ታምራት ወ/ማሪያም መሆናቸዉን የገለፁት በካፋ ዞን ፍትህ መምሪያ የታክስና ኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች ዐቃቤ ህግ አንዷአለም አሰፋ ናቸዉ።

እንደ ዐቃቤ ህግ አንዷአለም ገለፃ ተከሳሽ ታረቀኝ ቆጭቶ የተባለው በተጠቀሰው ቀን እና ሰዓት በዩንቨርስቲ ቀጠና ከቦንጋ ወደ ጊሞቦ ወረዳ በሚወስደዉ መንገድ ለመንገድ መብራት ተብሎ መሬት ዉስጥ የተዘረጋ 240 ሜትር የዋጋ ግምቱ አንድ መቶ ሰባ ሶስት ሺህ አራት መቶ ብር የሚያወጣ ከመሬት ቆፍሮ መስረቁን ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰዉ ጥቆማ ተከታትሎ መያዙን ተናግረዋል።

የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አድርጎ የምርመራ መዝገቡን በሰዉና በእግዚቭት ማስረጃዎች በማደራጀት ክስ እንዲመሠረትባቸዉ ለካፋ ዞን ፍትህ መምሪያ የታክስ እና ኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች ዐቃቤ ህግ የምርመራ መዝገቡን መላኩን ተናግረዋል።

በካፋ ዞን ፍትህ መምሪያ የታክስና ኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች ዐቃቤ ህግ አንዷአለም አሰፋ ሁለቱ ግለሰቦች ላይ ፖሊስ ምርመራ መዝገብ አደራጅቶ የላከዉን መዝገብ መርምሮ አንደኛ ተከሳሽ ታረቀኝ ቆጭቶ በኤፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1) ሀ እና የቴሌኮምንኬሽን እና የኤሌክትሪክ ኃይል አዉታሮችን ደህንነት ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 464/1997 አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 2 እና አንቀፅ 4ን ተላልፎ በመገኘቱ በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳት በማድረስ ክስ እንደተመሠረተበት ጠቅሰዋል።

ያገለገሉ ዕቃዎች ወይም በተለምዶ ቆራልዬ ተብሎ የሚጠራዉን የሚገዛዉ ሁለተኛ ተከሳሽ ታምራት ወ/ማሪያም ለህዝብ አገልግሎት የሚዉለዉን በዉድ የዉጭ ምንዛሪ የሚገባዉን የተሰረቀ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ሽቦ በ500 ብር በመግዛት በንግድ ድርጅቱ ዉስጥ ሸሸጎ በመገኘቱ በኢፌድሪ ወንጀል ህግ አንቀፅ 683 ለ እና ሐ ላይ የተደነገገዉን በመተላለፋ ዐቃቤ ህግ በመሸሸግ ወንጀል ክስ መመስረቱን አስረድተዋል።

የተከሳሾችን የክስ መዝገብ ሲመለከት የቆየዉ የካፋ ዞን ፍርድ ቤት ሰሞኑን በዋለው የወንጀል ችሎት 1ኛ ተከሳሽ ታረቀኝ ቆጭቶ በፈፀመዉ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት በማድረስና በስርቆት ወንጀል ጥፋተኝነቱ በመረጋገጡ በሶስት አመት ከሰባት ወር እስራት እንዲሁም የተሰረቀ ዕቃን በመግዛትና በመሸሸግ ወንጀል ጥፋተኛ በመሆኑ ሌሎችን ያስጠነቅቃል ወንጀል ፈፃሚዉን ያስጠነቅቃል በሚል 2ኛ ተከሳሽ ታምራት ወ/ማሪያም በአራት አመት ፅኑ እስራትና በአምስት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ዉሳኔ እንደተላለፈባቸዉ ዐቃቤ ህግ አንዷአለም አሰፋ ጨምረዉ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ዐቃቤ ህጉ የተሰረቀ ዕቃዎችን በመግዛት ሆነ በማስቀመጥ የተደረሰበት አካል በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን አዉቆ ምንጩ የማይታወቅ ዕቃዎችን ከመግዛት እንዲቆጠቡ አሳስቧል ሲል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *