



በ2017 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የገቢና ወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል የኮንትሮባንድና ድንበር ቁጥጥር መምሪያ የሬጅመንት 14 አዛዥ ኮማንደር ጌትነት አበዛ ፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታት እራሱን የቻለ የኮንትሮባንድ ቁጥጥር ፖሊስ አደራጅቶ ወደ ሥራ በማስገባት ቀድሞ ከነበረው የተሻለ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ኮንትሮባንድን የመያዝና የመቆጣጠር አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉን ገልፀዋል።
ሕገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት የሚያስከትልና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ በመሆኑ በየጊዜው የዝውውር ስልቶቹን በማጥናትና በመከታተል፤ ተሞክሮዎችን በመቀመር እና የመረጃ ሥራችንን በማጠናከር ከጉምሩክና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
