



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ፣ ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የማርበርግ ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ ለጤና ባለሙያዎች በቦንጋ እና ሚዛን ከተሞች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
ቢሮው በመጀመሪያ ዙር ከክልሉ ሁሉም ዞኖች ለተወጣጡ 3መቶ 29 የጤና ጣቢያ ኃላፊዎች እና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በበሽታው መተላለፊያ፣ መከላከያ እና መቆጣጠር እንዲሁም በበሽታው ምንነት ዙሪያ የተዘጋጀውን ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
በቦንጋ ማዕከል የስልጠናው ማስጀመሪያ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ፥ አቶ ኢብራሂም ተማም የማርበርግ ቫይረስን በመከላከልና መቆጣጠር ረገድ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል።
ክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የቫይረሱ ክስተት ከተመዘገበበት አከባቢ ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ስጋቱን ለመቀነስ እና በሽታውን ቀድመው ለመከላከል በልዩ ትኩረት እየተሰራ መኾኑን ነው የገለጹት።
ስልጠናው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በበሽታው ምንነትና በመተላለፊያ መንገድ ላይ በቂ ግንዛቤ በመውስድ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራውን በብቃት እንዲወጡ ያስችላልም ነው ያሉት አቶ ኢብራሂም።
በሽታውን ቀድመው ለመከላከል በክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል የድንገተኛ ጤና ችግር የሚከተታል ማዕከል EOC (Emergency Operation Center) የመረጃ ቅብብሎሽ ስርዓት በመዘርጋት በንቃት ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።
የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን በተገቢው እየተከላከሉ ተገቢውን የጤና አግልግሎት እንዲሰጡ በላብራቶሪ የናሙና አወሳሰድ፣ በመከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ ስልጠናዎች በየደረጃው እየተሰጠ እንደኾነም ነው ኃላፊው የገለጹት።
ከስልጠናው መልስ ባለሙያዎች የቤት ለቤት የቅኝት ስራዎችን በማጠናከር በተላይም በማኅበራዊ አግልግሎት ሰጪ ተቋማት ለኅብረተሰቡ በበሽታው መተላለፊያ መንገዶች ዙሪያ በስፋት ግንዛቤ መፈጠር እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ኢብራሂም በአጽንኦት ተናግረዋል።
የጤና ተቋማት ንጽሕና በመጠበቅ እና የኢንፌክሽን ቁጥጥር ተግባር በማጠናከር የበሽታ መከላከል ስራውን በየደረጃው የሚገኙ የጤና ተቋማት በቁርጠኝነት መደገፍ እንዳለባቸውም አቶ ኢብራሂም አስገንዝበዋል።
በሽታው ከተከሰሰበት አከባቢ የጉዞ ታሪክ ያላቸውና ከበሽታው ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ልየታና ክትትል ስራው ልዩ ትኩረት የሚሻ ተግባር መኾኑን ያመለከቱት አቶ ኢብራሂም ተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በሚዲያ አማራጮች በተላያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ እንደሚኾን ተናግረዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
