




የቤንች ሸኮ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ተመርቀዉ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በምረቃው ንግግር ያደረጉት የቤንች ሸኮ ቴሌቪዥን ቦርድ የበላይ ጠባቂና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፤ ዛሬ የተመረቀው የቤንች ሸኮ ቴሌቪዥን በ2013 ዓ.ም ሀሳብ ተጸንሶ ብዙ ውጣውረዶችን ተሻግረው ዛሬ ለምረቃ በቅቷል ነው ያሉት።
ዞኑ በተፈጥሮ ጸጋ የበለጸገ የመከባበርና የመቻቻል ባህል የጎለበተ አከባቢ ነው ያሉት አቶ ፍቅሬ አማን የአከባቢው ሚዲያ ባለመኖሩ በአግባቡ ያሉ ሀብቶች ሳይተዋወቁና የውጤቱ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷልም ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ቴሌቪዥን በሦስት ቋንቋዎች በቤንችና፣ ሸኮኛ እና በአማርኛ ለማህበረሰቡ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያሰራጭ በመሆኑ ከዞን አልፎ ለክልሉና ለሀገሪቱ ህዝብ የመረጃ ምንጭ በመሆን እንደሚያገለግልም አንስተዋል።
ቴሌቪዥን ጣቢያው ብሔራዊ ገዥ ትርክት እንዲገነባ፣ የማህበረሰቡ እርስ በእርስ ትስስር እንዲጠናከር የማህበረሰቡ ቱባ ባህሎች እንዲተዋወቅ በትኩረት እንዲሰራም አሳስበዋል።
ሚዲያ ማህበረሰቡን እያዝናና የተከታዩ ቀልብ የሚስብና የሚገዛ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ ማሰራጨት ይገባል ያሉት አቶ ፍቅሬ አማን፤ ዘመኑ የድጅታል ዘመን በመሆኑ በመረጃ አቀራረብ፣ ቀረጻ እና ጥራት በመበልጸግ ገለልተኛ እና ነጻ ሆነው ሥራውን ማከናወን ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል አቶ ፍቅሬ አማን።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የቤንች ሸኮ ቴሌቪዥን ዋና ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ ከፍትን ሚዲያ የሀሳብ ብዝሃነት በማስተናገድ ማህበረሰቡ ሀሳባቸውን እንዲያንሸራሸሩ ሚናቸው የላቀ ነው።
በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብ ለመፍጠር ሚዲያ የጎላ ሚና እንዳለውም የገለጹት አቶ ሀብታሙ ከፍትን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ጎልተው እንዲወጣም ትልቅ ሚና ይጨወታል።
የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲከፈት በየደረጃቸው ሀሳብ፣ ገንዘብና ጊዜያቸውን ጭምር በማዋጣት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት አቶ ሀብታሙ ከፍትን ምስጋና አቅርበዋል።
የቤንች ሸኮ ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ ብሮድካስት አገልግሎት ፍቃድ ያገኘ መሆኑን የገለጹት የቤንች ሸኮ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ አስፋ ቴሌቪዥኑ አማርኛን ጨምሮ በቤንችና ሸኮኛ ቋንቋዎች እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ለማህበረሰቡ መረጃዎችን እንደሚያደርስም ገልጸዋል።
የቴሌቪዥኑ ሥራ መጀመር የማህበረሰቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ ትፊቶችን እና በአከባቢው የሚከናወኑ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካ ሥራዎችን ጎልተው እንዲወጣም ሚናው የጎላ ነዉ ሲሉም ሥራ አስኪያጁ አንስተዋል።
በፍቅር ከበደ
