







በግብርና ኢንቨስትመንት ስራዎች ስትራቴጂክ በሆኑ የገበያ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚገባ ተገልጿል ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም( FSRP) ጋር በመተባበር ክልል አቀፍ የግብርና ኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከ3.91 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንደሚገኝ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
በክልሉ ያለው መሬት አብዛኛው ለእርሻ ስራ አመቺ መሆናቸውንና ከዚህም ውስጥ 52.2 ከመቶ የሚሆነው በግብርና ልማት ስራዎች የተሸፈነ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ አብራርተዋል ።
ለአልሚ ባለሀብቶች ተላልፈው ከነበሩ 482 የግብርና ፕሮጀክቶች 67.5 በመቶ መሬት መልማቱና ቀሪው አለመልማቱን ባቀረቡት የውይይት ሰነድ አቅርበዋል ።
በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት አቶ ተመስገን በ2016 በጀት ዓመት ብቻ 16 ቢሊዮን ካፒታል መመዝገቡንም አብራርተዋል ።
በክልሉ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ከወሰዱት መሬት አብዛኛውን ወደ ልማት አለማስገባታቸውና ለዚህም መሠረታዊ የሆኑ ችግሮችን በጋራ በመወያየት መፍትሔ ማፈላለግ ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም አመላክተዋል።
በኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ አለማየሁ ገ/ስላሴ በክልሉ ከሚገኙ 430 የግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ ባለሀብቶች በ315 ቱ ላይ ተደራሽ በመሆን የባለሀብቶችን በቴክኖሎጂየታገዘ ዘመናዊ የመረጃ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ባለድርሻ አካላት በነበረው ውይይት ከልማት ስራዎች ጋር በተያያዘ ችግሮች ያሏቸውን ሀሳቦች አንስተዋል።
ተሳታፊዎቹ በልማት ስራዎች የብድር አቅርቦት ፍትሐዊና ተደራሽ አለመሆን ፣የመሠረተ ልመሠት አቅርቦት ችግሮችና ሌሎች መሰል ችግሮችን አንስተዋል።
በተሰማሩበት የልማት ስራዎች ጥራትን በጠበቀ መልኩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማልማት ችግሮቻችንንም ወስደን መሬቶቻችንን ማልማት ከራስ የሚጠበቅ ተግባርም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ለአልሚ ባለሀብቱ ተገቢው የባንክ ብድር አገልግሎት በፍትሐዊነት ሊመቻች እንደሚገባ አሳስበዋል ።
ባለሀብቱ በተሰማራበት የልማት መስክ ጥራትን የጠበቀ እሴት የጨመረ ሀብት በማልማትና ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የመሠረ ልማት ችግሮችና ሌሎች መሰል ችግሮችን በመቅረፍ አልሚው ባለሀብት ውጤታማ እንዲሆን በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል ።
በኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት እና ግብኣት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ሶፊያ ካሣ የጋራ የሆኑ ችግሮቻችንን በጋራ በመፍታት የሚጠበቀውን ልማት በተገቢው ማምጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የግሉ ባለሀብት ወደ ግብርና ልማት ሲገባ የአካባቢውን ማህበረሰብ የሚቀይሩ ስራዎችን መስራት በቡና ልማትና በኤክስፖርት ምርቶች ጥራትን በማስጠበቅ ገበያን በማረጋጋት ልማቱን በሙሉ አቅሙ ማልማት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል ።
በክልሉ በሚመረቱ ምርቶች ብራንዲንግ /አካባቢያዊ ስያሜ/ በመስጠት ለገበያ ማቅረብ ከአልሚው ባለሙያ የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በሰጡት ማጠቃለያ ሀሳብ መንግስት እና ባለሀብቶች ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት ሁሉም ሚናውን መወጣት ይገባል ብለዋል።
አልሚው ባለሀብት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ማንሳቱ ተገቢ መሆኑንና ችግሮችንም በተቀናጀና በተናበበ መንገድ እየፈታን ልማቱን በሙሉ አቅም በማልማት ወደ ምርት መግባት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የሜካናይዜሽን እርሻዎችን በማጠናከር ጥራትና እሴት ጨምሮ ማልማት እንዲሁም በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ አልሚ ባለሀብቱ ትኩረት በመስጠት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ ።
ባለሀብቱ የሚጠይቃቸው የባንክ ብድር አገልግሎት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለአልሚው ባለሀብት ተደራሽ እንዲሆን ያለውን የአሰራር ክፍተት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንዲፈታ ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል ።
በኢንቨስትመንት ልማት ዘርፎች ስትራቴጂክ በሆኑ የገበያ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚገባም ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳስበዋል ።
በአልሚ ባለሀብቱ የተዘጋጁ የተለያዩ የልማት ስራዎች ኤግዚቢሽን በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የተመራው ልዑክ ጉብኝት አድርጓል ።
በነበረው የአልሚ ባለሀብቱ ውይይት በተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሾችን በመስጠት መድረኩ ተጠናቅቋል ።
በታጠቅ አበበ
