
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ ጥራትና ብቃት ያላቸውን መምህራን አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማሰማራት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ገልጸዋል።
ትምህርት ቢሮው ከቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ጋር በመተባበር በ2017 የትምህርት ዘመን በዲፕሎማና በሰርተፍኬት መርሃግብር 730 ዕጩ መምህራንን ተቀብሎና በብቃት አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማሰማራት ምዝገባ መጨረሱንም ሀላፊው አብራርተዋል።
ከ730 ዕጩ መምራን መካከል 110 በአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ለማሰልጠን መታቀዱ በክልሉ የሚስተዋለውን የአፍ መፍቻ ቋንቋ መምህራን እጥረት ለመቅረፍ እንደሚያግዝም ተገልጿል።
በዲፕሎማና በሰርተፍኬት 730 መምህራን አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማሰማራት በወጣው ማስታወቂያ 2927 ተወዳዳሪዎች መመዝገባቸው በክልሉ በመምህርነት ሙያ ለመሰማራት ያለው ፍላጎት መጨመሩን ያሳያል ተብሏል።
ለተመዘገቡ ተወዳዳሪዎች ህዳር 20/2017 ዓ.ም በክልሉ በስድስቱም ዞኖች በተዘጋጀው የፈተና ቦታዎች የቃልና የፅሁፍ ፈተና እንደሚሰጥም ታውቋል።
ለዕጩ መምህራን የሚሰጠው ስልጠና ከአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ጋር የተጣጣመ እንደሆነም ተብራርቷል።
የትምህርት ዘርፍ ውጤታማነትን ለማረጋጉጥ በመምህራንና በትምህርት አመራር ልማት ላይ የሚሰራ ሪፎርም ወሳኝ ነው ያሉት የቢሮው ሀላፊ ከዚህ ጋር በተያያዘ የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ አመራሮችን መልሶ ለማደራጀት እየተሰራ ያለው ተግባር ወደ መጠናቀቅ እንደደረሰም አስረድተዋል።
ነባር የኮሌጁ አመራሮችን ጨምሮ አዳዲስ ዕጩዎች ተወዳድረው ወደ አመራርነት እንዲመጡ በወጣው ማስታወቂያ መሠረት 28 ዕጩዎች መመዝገባቸውም ተገልጿል።
ዕጩዎችን ለመለየት በቢሮ ምክትል ሀላፊ የሚመራና ሌሎች የባለድርሻ አካላትን ያካተት መልማይ ኮሚቴ ተደራጅቶ በርካታ ስራዎች ስሰሩ መቆየቱም ተነግሯል።
የተቀመጡ መመዘኛዎችን ያለፉ ዕጩዎች ህዳር 18 እና 19/2017 ዓ.ም የኮሌጁን የቀጣይ አምስት አመታት ስትራቴጅክ ዕቃዳቸውን የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የባለድርሻና ሌሎች ገለልተኛ አካላት በተገኙበት እንደሚያቀርቡም ታውቋል።
ቢሮው በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ሪፎርምን ተግባራዊ በማድረግ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳዳግ የባለድርሻ አካላትንና ህብረተሰቡን በማስተባበር ሰፊ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አቶ አልማው አስረድተዋል
