


የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ክፍል በኢትዮዽያ በሥራ ላይ ካሉ ታላላቅ አለምአቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የውጭ ጋዜጠኞችን ሚዛናዊ እና ተጨባጭ የዘገባ ሽፋንን ለማሳደግ አላማ ያደረገ ውይይት አካሂዷል።
ኢትዮጵያ ፈጣን የለውጥ እና ልማት ሂደት ውስጥ እንደመገኘቷ ጋዜጠኞች የተጠራ መረጃ ብሎም ዝርዝር ግንዛቤ ማግኘታቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። መሰል ግንኙነቶች በኢትዮዽያ ላይ ያተኮሩ የዜና ሽፋኖች የኢትዮጵያን እድገት የሚያንፀባርቁ፣ ለፈተናዎቿ እውቅና የሚሰጡ ብሎም መንግሥት ለአካታች እድገት እና ዘላቂ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ እንዲሆኑ ያግዛሉ።
አፍሪካ በአለምአቀፋዊው ሚዲያ የምትሸፈንበት ትርክት በአብላጫው በበሽታ፣ በድህነት፣ በግጭት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት መልኮች ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ምስልም በአለምአቀፍ ደረጃ ስለአፍሪካ ያለውን አመለካከት እና የፖሊሲ ውሳኔ እየቀየሰ ቀጥሏል።
በመሆኑም የዛሬው ውይይት ሚዛናዊ እና ምሉዕ እይታ ያለው የዘገባ ሥራን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥቶ የተነጋገረ ለወደፊቱም ለዚህ አይነቱ አዘጋገብ መጠናከር መንገዶችን የተመለከተ ነበር ሲል ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
