






የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዘርፍ ከዞን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አስተባባሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር የክልሉን ምዝገባ ስርዓት ለማሳደግ የምርጥ ተሞክሮ ልምድ ልውውጥ በካፋ ዞን ዋቻ ከተማ አካሂደዋል፡፡
በፕሮግራሙ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ዓለሙ ሁልጊዜ መናበብ ፣ መደማመጥ እና ቅንጂታዊ አሰራር ሲኖር ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ጠቁመው ለዚህም ዋቻ ከተማ አስተዳደር ትክክለኛ ማሣያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
በታችኛው መዋቅር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እጅግ ፈታኝ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ ስራው ውጤታማ እንዲሆን የዋቻ ከተማ አስተዳደርን የምርጥ ተሞክሮ በመውሰድ በኃላፊነት እና በቁጭት መምራትና ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል ፡፡
የክልሉ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ደነቀ በበኩላቸው ሁሉም ዜጋ የሚታወቅበትን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው ለዚህም እንደ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ውጤታማ እንዲሆን በርካታ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩና ለውጦች ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ውጤታማ እንዲሆን ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠንከር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ህብረተሰቡ የመመዝገብ ባህሉን እንዲያዳብር አሳስበዋል፡፡
የዋቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የወሳኝ ኩነት ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሁነኛው ታደሰ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጀ ዜግነትን መሠረት ተደርጎ እየተሰራ ያለው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በዋቻ ከተማ ደረጀ በልዩ ትኩራት እየተሰራ ያለ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዜጎች መብቶቻቸውን ለማስከበርና ግዴታቸውን ለመወጣት እንዲያስችል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከተጀመረ አንስቶ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡
በ2015 ዓ/ም በሁሉም የኩነት አይነቶች ዝቅተኛ አፈጻጸም እንደነበር አስታውሰው በበጀት ዓመቱ ከዚህ ውድቀት ለመነሳት አደረጃጀቶችን በማጠናከርና በቅንጅት በመስራቱ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል።
የዋቻ ከተማ አስተደር ምክትል ከንቲባ እና ፍትህና መልካም አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማቲዮስ ጋኖ የከተማ አስተዳደሩን አፈፃፀም እና ዕቅድ ለመድረኩ ለተሞክሮ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም ሰለ ወሳኝ ኩነት ዝቅተኛ ግንዛቤ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ በጋራ በመሰራቱ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በ2016 ዓ/ም በሁሉም ኩነቶች 1ሺህ 80 ለመመዝገብ ታቅዶ 1ሺህ 9 መቶ 48 ኩነቶችን ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
ይህም አፈጻጸሙ 180 ፐርሰንት መሆኑን አብራርተው በ2017 በጀት ዓመት 1ሺህ 80 ኩነቶችን ለመመዝገብ መታቀዱን አብራርተዋል።
መድረኩ በ2016 በጀት ዓመት ዋቻ ከተማ አስተዳደር ከ02 ቀበሌ በወሳኝ ኩነት የተሻለ አፈጻጸም በማስመዘገቡ የምርጥ ተሞክሮ ልምድ ልውውጥ ተደርጓል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላት በበኩላቸው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ውጤታማ የሚያደርግ የምርጥ ተሞክሮ ልምድ ልውውጥ ማግኘታቸውን አንስተው በቀጣይ ወርደው ለማስረዳት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የወሳኝ ኩነቶች ዘርፍ ለአቅም ደካማ ተማሪዎች የሚሆን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል ፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
