






የመንግሥት ተቋማት ለህዝቡ የሚሰጡት አግልግሎት ጥራትና ፍትሀዊ ተደራሽነትን ያረጋገጠ መሆን እንዳለበት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ።
የክልሉ ጤና ቢሮ የመንግሥት የጤና ተቋማት አግልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ያተኮረ ክልላዊ ንቅናቄ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ በተገኙበት በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በመንግሥትና መሪው የብልጽግና ፓርቲ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ከሚገኙ ተግባራት አንዱ በየደረጃው የሚታይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት መሆኑን የገለጹት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ የመልካም አስተዳደር ችግር መጠኑ ብለያይ እንጂ በሁሉም ደረጃ፣ በሁሉም ተቋማት የሚታይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት ከሚስተዋልባቸው ተቋማት አንዱ የጤና ተቋም መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ችግሩን በጋራ ቅንጅት በመፍታት የጤና አግልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግር በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ባለፉት ጊዜያት የክልሉ መንግሥት የጤናው ዘርፍ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ማሻሻያ ተግባራትን ስያደርግ እንደቆየ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ይሁን እንጅ ከችግር ስፋትና ውስብስብ ባህር አኳያ በተሟላ መልኩ ማረጋገጥ ያልተቻለ በመሆኑ ሁሉም የጤናው ዘርፍ አመራር ተግባሩን በልዩ ትኩረት በመምራት ተግባሩን በቁርጠኝነት ማሳካት ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የጤና መድኃን ሽፋን ለማሳደግ በተሰራው ውጤታማ ተግባር በአጭር ጊዜ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ይህን ውጤታማ ተግባር ተሞክሮ በመቀመር በሌሎች የጤና አግልግሎት ዘርፍም መድገም እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
መደበኛ የጤና አግልግሎት ለማሻሻል በከተሞች የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት በማቋቋም አግልግሎትን ማሻሻል እንደሚገባ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ለማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የተሰበሰበው ሀብት ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል የአሰራር መመሪያ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መገባት እንዳለበትም በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
የመክፈል አቋምና ያገናዘበ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የአባላት ምጣኔና የመዋጮ አሰባሰብ በክልሉ ውጤታማ እንደነበረ የገለጹት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ተሰብስበው ወደ ባንክ ያልገቡ ገንዘብ ጉዳይ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥራቱን የጠበቀ እና ፍትሃዊ የሆነ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ማድረስ፣ዓላማ ያደረገ ጥረት የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስገኝ የባለሙያውና የአመራር ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር እንዳለበት የገለጹት አቶ ኢብራሂም የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ለተሻለ ውጤታማነት መስራት ይገባል ብለዋል።
በጤና ተቋማት የሚሰጡ አግልግሎት ችግሮችን በመለየት ተገቢውን ማሻሻያ ተግባራዊ ይደረጋል ያሉት አቶ ኢብራሂም በሂዴቱ ተጠያቂነትን የማስፈን እና በህዝቡ ዘንድ ባለቤትነት የማረጋገጥ ተግባር እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በመድረኩ የተለያዩ ሰነዶች እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የአፈፃፀም ሪፖርት ቀርበው ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።
በዚህ የንቅናቄ መድረክ የክልልና የዞን የፊት አመራሮች እንዲሁም የጤናው ዘርፍ የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።
በዕድገቱ በዛብህ
