የበጎነት ተግባር የማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሴቶች ክንፍ፣ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወሰን ተሻጋሪ የበጎ አድራጎት ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

የጽ/ቤቱ የሴቶች ክንፍ ኃላፊ ወ/ሮ ሰብለጸጋ አየለ እንደገለጹት፣ የበጎነት ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበቱ መምጣታቸው በዜጎች መካከል ያለውን ማህበራዊ ትስስርና የቤተሰባዊነት ስሜት ያጠናክራል። በመሆኑም ለእንዲህ ዓይነት ተግባራት ቀጣይነት በጋራ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።

ለዚህ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ አድራጎት ሥራ ከ385 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ሀብት ከየደረጃው ከሚገኙ መዋቅሮች ተሰባስቦ ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መላኩን ኃላፊዋ ተናግረዋል።

ይህ ድጋፍ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለሚገኙና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የተበረከተ ሲሆን፣ በተለይም ለተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች፣ የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶች፣ የቤት መስሪያ ቁሳቁሶች እንዲሁም የምግብና የአልባሳት ድጋፎችን ያካተተ ነው። ይህ እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ከጎናቸው መቆሙን በተግባር ለማሳየት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ሥራ መከናወኑን የጠቆሙት ወ/ሮ ሰብለጸጋ፣ ድጋፉ የዜጎችን ችግር ከመቅረፍ ባለፈ ኢትዮጵያዊ ቤተሰባዊነትን፣ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትንና ትስስርን ለማጠናከር እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

በመጨረሻም ይህ በጎ ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረው በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ለተደረገው ድጋፍ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በካሳሁን አሰፋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *