


የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸዉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ድርጅት የዘር ብዝዬት ስራን በኮንታ ዞን በይፋ አስጀምረዋል።
ድርጅቱ በኮንታ ዞን ኮይሻ ወረዳ በቡላ ሀማኮ ቀበሌ በ10 ሄክታር ማሳ የማሾና የቦለቄ መስራች ዘር በማባዛት ነው ስራውን የጀመረው።
ድርጅቱ በክልሉ የመስተዳድር ምክር ቤት ደምብ ቁጥር 8/2015 በአዋጅ ተቋቋሞ በ2015 በጀት ዓመት ማገባደጃ ወደ ስራ መግባቱ የተገለጸ ሲሆን ከክልሉ መንግሥት የተመደበለትን የ20 ሚሊዮን መነሻ ካፒታል እና 4 የእርሻ ትራክተሮችን በመያዝ ከሶስት ወራት በፊት ወደ ሥራ መግባቱ ተመላክቷል።
የክልሉ መንግሥት የአርሶአደሩን ህይወት በዘላቂነት ለማሻሻል ባለው ቁርጠኛ አቋም ይህንን የልማት ድርጅት ማቋቋሙን የገለጹት የምርጥ ዘር ድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የግብርና ሥራን ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የምርጥ ዘር አቅርቦት ወሳኝ መሆኑ ነው ብለዋል።
በክልሉ የሚስተዋለው የምርጥ ዘር እጥረት በምርትና ምርታማነት ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ጫና ለመቋቋም የክልሉ መንግሥት የልማት ድርጀቱን አቋቋሞ ወደ ስራ ማስገባቱን ነው አቶ ማስረሻ የተናገሩት።
ለግብርና ሥራ መሠረታዊ ከሆኑ ግብዓቶች አንዱ የምርጥ ዜር መሆኑን የተናገሩት የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነጋ አበራ በምርጥ ዜር ድርጅት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች የአርሶአደሮች የዜር አቅርቦት ችግር ይፈታል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸው ተናግሯል።

አቶ ነጋ አክለው የዞኑ አስተዳደር ለዘር ብዜት የሚያስፈልገውን የእርሻ ማሳ ከማቅረብ ጀምሮ ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ድርጅቱ ከክልሉ ስነምህዳር ጋር ተስማሚ የሆኑ የሰብል ምርጥ ዘር በራሱ፣ በአርሶአደርና በባለሀብቶች ማሳ የመስራች ዘር ብዜት ለማባዛት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ እምሩ ወየሳ ተናግረዋል።

በኮንታ ዞን ለምርጥ ዘር ድርጅቱ 3 ሺህ
ሄክታር መሬት የተሰጠ ሲሆን በሌሎች ዞኖችም የመሬት አቅርቦቱ ተመቻችቶ ወደ ሥራው ለመግባት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
በወረዳው ለመካናዝድ እርሻ የሚሆን ሰፊ መሬት መኖሩ የገለጹት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማርቆስ ወንድሙ የወረዳው አስተዳደር ለምርጥ ዜር ድርጅት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
