የበጀት ዓመቱ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ና የሌማት ትሩፋት ስራዎች ንቅናቄ መድረክ ተጀመረ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ክልላዊ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስራዎች የ2015 አፈጻጸምና የ2016 ዕቅድ የንቅናቄ እንዲሁ የሌማት ትሩፋት ተግባራት አፈጻጸም የሚገመግም መድረክ በቦንጋ እየተካሄደ ይገኛል።

ክልሉ ለእርሻ ስራ አመቺ የሆነ የአየር ፀባይና ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት እንዲሁም በቂ የከርሰምድርና ገጸምድር የውሃ ሀብት ያለው መሆኑን የገለጹት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር፣ ያሉ ዕድሎችን ወደ ሀብት መቀየር እንዲሁም የልማት ሠራተኞችን አቅም መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል።

በክልሉ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ስራ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ተግባሩን በማስፋት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠር እንደሚገባም የተነሳ ሲሆን የካፋ ዞን በዚህ ረገድ የተሻለ ተግባር መፈጸሙ በመድረኩ ተነስቷል።

በ2016 በጀት ዓመት በሌማት ትሩፋት ፓኬጅ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፈጠር የታቀደ ሲሆን የከተማ አስተዳደር መዋቅሮችና የማዘጋጃ ከተሞች የመሸጫ ሼዶችን እንዲያመቻቹ ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ጠይቀዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊና አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው የግብርና ስራ ከቤተሰብ ፍጆታ አልፎ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በመፍጠንና በመፍጠር በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ነው የገለጹት።

ዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ የቆየውን የግብርና ስራ በመስኖ አማራጮች ማስፋት እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ማስረሻ ያሉንን የውሃ አማራጮች አሟጦ መጠቀም ይገባልም ብለዋል።

አቶ ማስረሻ አክለው በሌማት ትሩፋት የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።

በክልሉ በ2015 በጀት በ3ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ የበጋ ስንዴ ማምረት መቻሉ ተገልጿል።

ውጤቱ የተመዘገበው በጠንካራ የአመራርና ባለሙያዎች ቅንጅት መሆኑ ተመላክቷል።

በንቅናቄው መድረክ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከስድስቱም ዞኖች የሚመለከታቸው የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *