የዘንድሮ የካፈቾ ዘመን መለወጫ “ማሽቃረ ባሮ” በዓልን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

Spread the love


ኢትዮጵያ ሀገራችን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች የታደለች ነች። የተለያየ ቋንቋና ባህል ያላቸው ህዝቦች ተዋደው፣ ተከባብረውና ተጋምደው የሚኖሩባት ሀገር ናት።
አገሪቱ ያሏት ባህላዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎች የህዝቦቿ የማንነት መገለጫ መሆናቸውም በሰፊው ይናጋራል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚገኙ 13 ነባር ብሔር ብሔረሰቦች መካከል የካፈቾ ብሔር አንዱ ነው፡፡
የካፈቾ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን መለወጫ በዓል “ማሽቃረ ባሮ” በመባል ይታወቃል፤ ይህም የዘመን ለውጥ የክረምት ወቅትን ተከትሎ በብሔሩ አቆጣጠር መሠረት በየዓመቱ ይከበራል።
በክረምቱ ወቅት በካፋ ምድር የሚገኙ ወንዞች ይሞላሉ፤ የካፋ ህዝብ የማሽቃረ ባሮ አዲስ ዓመት ከገበሬው የእርሻ ስራ ጋር የተያያዘ ሲሆን መለያውም ከመዝራት፣ ከእድገት እና ከመኸር ዑደት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይነገራል።
የብሔሩ አባላት በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚያከብሩት ትውፊታዊ ይዘት ያለው የዘመን መለወጫ በዓልም ነው፡፡
የካፋ ንጉስ መቀመጫ በነበረውና በየዓመቱ በዓሉ በሚከበርበት “ቦንጌ ሻንቤቶ” በሚባለው ስፍራ በዓሉ ሲከበር በዞኑ የሚኖሩ ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያሳይ ስነ ስርዓት ያካሂዳሉ፡፡
ይህ በዓል የካፈቾ ብሔር አባላት በጉጉት የሚጠብቁት ከአሮጌው ወደ አዲሱ ዓመት የሚሸጋገርበት አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት ህዝባዊ በዓል እንደሆነ ይነገርለታል፡፡
የካፋ ዞን ባህል፣ ቱርዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ነፃነት ብርሃኑ የካፈቾ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል “ካፈች የበነ ሻደ ማሽቃረ ባሮ” በዓል ከ1897 በፊት በነበሩት በካፋ ነገስታት ዘመን በየዓመቱ ከሁሉም ወራፎዎች ወደ ቦንጋ ከተማ ቦንጌ ሻምበቶ በመምጣት በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያከብሩ ነበር ብለዋል።
ከ1897 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሳይከበር የቆየና አሁን በተፈጠረው ምቹ ዕድል ከ1998 ዓ.ም ጀሞሮ በድጋሚ በየዓመቱ እየተከበረ መጥቷል ብለዋል አቶ ነፃነት።
በበዓሉም በዓመቱ ውስጥ የተሰራ ስራ የሚገመገምበት፣ አዳዲስ ሹመት የሚሰጥበት፣ የተሰጠውን ሀላፊነት በአግባቡ የማይወጣ የሚወርድበት እና በበዓሉ ላይ የተገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በልተውና ጠጥተው ጠግበው የሚሄዱበት ወቅት የነበረበት መሆኑን ነው የበዓሉ አዘጋጅ አብይ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ነፃነት ብርሃኑ ያብራሩት።
የበዓሉ አከባበር ስርዓት ሐምሌ 5 መነሻ በማድረግ የሚቆጠር ስሆን 77 ቀን እየተባለ ሄዶ እየተቆጠረ 77ኛው ቀን ሲያልቅ የሚከበርበት የአዲስ ዓመት አከባበር ስርዓት እንዳለው ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በዓሉ በካፈቾ ብሔር ዘመን አቆጣጠር መሠረት ዓመት አልፎ ዓመት የሚተካበት አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ ተደርጐ ስለሚወሰድ በከፍተኛ ደስታ የሚከበር የመሸጋገሪያ በዓል ነው ያሉት አቶ ነጻነት የ2017 የካፈቾ ዘመን መለወጫ በዓልን ከዚህ ቀደም ከሚከበረው በላይ ለማክበር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም በዓሉን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል አብይ ኮሚቴና የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን ተዋቅረው ወደ ስራ መገባቱንም የጠቆሙት አቶ ነፃነት በዓሉን በተሳካ መንገድ ላማክበር የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሀብት የማሰባሰብ ስራ የተጀመረ መሆኑን ተናግረዋል።
በየዓመቱ የሚከበረው የብሔሩ ዘመን መለወጫ በዓል በቋንቋና ባህል እድገት ላይ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ከማድረግ ባለፈ በዞኑ የቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅ ምቹ መንገድ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
ስለሆነም የካፈቾ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል የካፋ ህዝብ ለሀገርና ለዓለም ያበረከተው ድንቅ ባህላዊ እሴት ነው ማለት ይቻላል ያሉት አቶ ነፃነት ብርሃኑ በዓሉንም በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚያስችል ሰፊ እንቅስቀሴዎች እየተደረጉ መሆኑንም አብራርዋል፡፡
የዘንድሮው የካፈቾ ዘመን መለወጫ በዓል ፍፁም አንድነትና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ከመስከረም 13 እስከ 14 በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ገልፀዋል፡፡


በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *