
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልል መንግስት በሚገኙ ዞኖች የወባ በሽታ ወረርሸኝን ለመቆጣጠር በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ፡፡
እንደ ሀገር ወረርሽኙ በስፋት በሚታይባቸው ክልሎች በክላስተር የተደራጀ አሰራር በመዘርጋት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲያስችል ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ በቅርቡ በማካሄድ ወደ ስራ ተገብቷል ፡፡ይህንን አደረጃጀት ተከትሎም በክልሉ የተከሰተውን የወባ በሽታ ወረርሽን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከፌዴራል ጀምሮ በተዋረድ እስከ ወረዳ ያሉ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የተቀናጀ አሰራር በመዘርጋት ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ እንደሚያመላክተው ወቅታዊ የወባ ወረርሸኝን ለመቀልበስ የጤና ፕሮግራምና የጤና ሥርዓት በማጠናከር በክልሉ ሁሉም ዞኖች ፣ወረዳዎች ፣ጤና ተቋማት እና በጤና ኬላ የሚሰሩ የጤና ኤክስቴንሸን ባለሙያዎችን ያሳተፈ ግምገማ ነክ ሰልጠና መድረክ በሶስት ማዕከል በማካሄድ እና ድጋፋዊ ክትትል ስራዎችን በማጠናከር የጤና ኤክስቴንሸን ፕሮግራምን በማነቃቃት የጤና ኤክስቴንሸን ባለሙያዎች ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል።
የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ አተገባበር ላይ በመሰረታዊ የጤና ኬላዎች ላይ አንዳንድ ባለሙያ በመመደብ የህክምና አገልግሎት መስጠት ተጅምሯል። ወረዳዎችም በጀት በመመደብ ሁሉአቀፍ ጤና ኬላዎች ግንባታ ስራዎች መጀመራቸውንም የቢሮው መረጃው ይገልጻል ፡፡
በክልሉ ጤና ቢሮ የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍና ምክትል ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ኃይሌ ዘውዴ ለክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በሰጡት መረጃ 194 የጤና ባለሙያዎችና የጤና ኤክስቴንሸን ባለሙያዎች በወባ ምርመራና ህክምና ላይ ስልጠና ወስደው ወደ ተግባር ገብተዋል ብለዋል ፡፡126 የላቦራቶሪ ባለሙያዎችም የወባ ምርመራና ጥራት ላይ ስልጠና መውሰዳቸውንና ለወባ ምርመራ የሚያገለግሉ ሪኤጄንትና ግብዓት ለጤና ተቋማት መሰራጨቱን አመላክተዋል ።
የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የተጀመረውን ተግባር ውጤታማ ለማድረግ በምክትል ቢሮ ኃላፊዎችና ዳይሬክቶሬቶች የሚመራ የባለሙያ ቡድን በሁሉም ዞን ስምሪት በመውሰድ በክላስተር ተመድበው ከመጡ የፌደራል ቡድን ጋር በቅንጂት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ኃይሌ ገልጸዋል ።
ህብረተሰቡን እየጎዳ የሚገኘውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከል እንደ ክልል ፖለቲካዊ ትርጉም በመስጠት በተዋረድ ከሚገኙ ምክር ቤቶች፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከክልል ትምህርት ቢሮ፣ ከክልል ግብርና ቢሮ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ኃይሌ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎችን በማቀናጀት ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና ማዳፈን እንዲሁም ቤት ለቤት የአጎበር አጠቃቀም ላይ የጋራ ዕቅድ በማዘጋጀት የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም አብራርተዋል ፡፡
በወባ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ አኳያ በጤና ተቋማት ዘወትር ከሚሰጠው የጤና ትምህርት በተጨማሪ የወባ መልዕክቶችን ተደራሸ ለማድረግና በክልሉ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ቋንቋዎች መልዕክት ቀርጾ ማስተላፍ እንዲቻል በክልሉ ባሉ ሚዲያዎች በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በቦንጋ፣ በሚዛን ፣ በዋካ እና በማሻ ቅርንጫፍ ፣በሚዛን ፋና ፣በካፋ ቲቪ፣ በቦንጋ ማሀበረሰብ ሬዲዮ እንዲሁም በኢዜኣ እና በክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ድረ-ገጽ ትምህርት ሰጪ የወባ መልዕክቶች እንዲተላለፉ እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል ።
እንደ ክልል እስካሁን በተደረገው የተቀናጀ አሰራር 140 ሺህ 965 አጎበር ማሰራጭት የተቻለ ሲሆን በስምንት ወረዳዎች ውስጥ ካሉ 166 ቀበሌዎች መካከል በ66 ቀበሌዎች የቤት ለቤት ኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ስለመሆኑ አቶ ኃይሌ ገልጸዋል ።
85 ሺህ 569 ዩኒት ስትራክቸር ለመርጨት ከሚጠበቀው ውስጥ 80 ሺህ 756 ዩኒት ስትራክቸር መርጨት የተቻለ ሲሆን አፈጻጸሙም 94.38% ማድረስ እንደተቻለም አብራርተዋል ።
በክልሉ ቀደም ብሎ በተለዩ ጊዜያዊና ቋሚ የወባ መራቢያ ቦታ ላለባቸው 54 ወረዳዎችና ከተማ አሰተዳደሮች 1,989,300 ሚሊ ሊትር የወባ ትንኝ ዕጭ መግደያ ኬሚካል የተላከ ሲሆን 1,750,652 ሚሊ ሊትር ኬሚካል ጥቅም ላይ ውሏል ሲሉም ገልጸዋል ፡፡
የህክምና አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሸ ለማድረግ ከዚህ በፊት የወባ ምርመራና ህክምና በማይሰጡ ጤና ኬላዎች የወባ ምርመራና ህክምና እየተሰጠ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም 959,944 ሰዎች ተመርምረው 538,327 (56%) የወባ የመያዝ ምጣኔ መኖሩን ያመላከተው የቢሮው መረጃ በዚህ ሁለት ሳምንት በተደረገው ንቅናቄ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው 165,886 ሰዎች ወባ የተገኘባቸውና የመገኘት ምጣኔው 65.7% መሆኑን አስረድተዋል ።
129,875 ሰዎችን መመርመር የሚያስችል ፈጣን የወባ መመርመሪያ ኪት፣ ለ299,230 ተመላላሸ ታካሚዎችን ማከም የሚያስችል ኮዓርተም እንዲሁም ለ1,848 ተኝተው ለሚታከሙ ሰዎች የሚሆን ግብዓት እስከ ጤና ኬላዎች ድረስ ማድረስ ተችሏልም ብለዋል።
በክልሉ ሁሉም ዞኖች ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ማህበረሰቡ ጥቆማ ማቅረብ የሚችልበትን ሥርዓት በመዘርጋት በኢትዮጲያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ያልተመዘገበና ያልተፈቀደ መድኃኒት በህዝብ ጥቆማ ተይዞ በህግ የማጣራት ስራዎች እየተከናወኑም እንደሚገን አቶ ኃይሌ ተናግረዋል
አጠቃላይ እንደ ክልል በተደረገው የወባ ወረርሸን መከላከል እንቀስቃሴ በቀን እንደክልል ሲስተናገድ ከነበረበት 7,000 (ሰባት ሺህ) የወባ ታማሚ በተደረገው ርብርብ አሁን ላይ ከ3,000 እስከ 5,000 (አምስት ሺህ) ማድረስ ተችሏል ሲሉም ገልጸዋል ።
በክልሉ መንግስት በሽታውን ለመከላከል የተሰጠውን ትኩረት ባለድርሻ አካላት እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የጤና አመራርና ባለሙያዎች የወባ ወረርሸኝ ለመቆጣጠር እስካሁን ያደረጉትን ርብርብ አተናክረው እንዲያስቀጥሉ በየአካባቢው ያሉ ህብረተሰብ ከፍሎችም ተባብረው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
በታጠቅ አበበ
