
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በዘንድሮ የበጋ ወቅት 225 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ለማካሄድ የንቅናቄ ስራ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ ለኢዜአ እንደገለፁት፥ በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ተራቁቶ የነበረ መሬት አገግሞ ለእርሻ ስራ መዋል ጀምሯል።
በለማው ስፍራ ወጣቶች ተደራጅተው በፍራፍሬና ንብ ማነብ ስራ ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘንድሮም ይህን ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል የንቅናቄ ስራ መጀመሩንና ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ለ30 ቀናት የሚቆየው የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ እንደ ክልል ጥር 22 በይፋ እንደሚጀመርና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለማሳተፍ መታቀዱን ገልጸዋል።
በዘንድሮ የበጋ ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተለዩ 1 ሺህ 100 ንዑስ ተፋሰሶች 225 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ስራ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት፣ለልማቱ የሚሆኑ መሳሪያዎችና የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመለየት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
“ባለፉት ዓመታት የተገኙ ተሞክሮዎችን በማስፋትና ጉድለቶችን በማረም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የተጠናከረ ስራ ይሰራል” ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በበጋ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተፋሰስ ልማት ከ1 ሺህ በሚበልጡ ንዑስ ተፋሰሶች ለከ217 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን አስታውሰዋል።
