
በመጀመሪያዉ የብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ ከተቀመጠው ዉሳኔ መነሻ በክልሉ ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች ለማህበራዊ፣ኢኮኖሚዊ እና ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ምቹ መደላድሎች መፈጠራቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ሰላምና ፀጥታ አስተዳዳር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ገለጹ።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳዳር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ፤ ብልጽግና ፓርቲ በአንደኛው መደበኛ ጉባኤ ካስቀመጣቸው ውሳኔዎች እና ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ የተተገበሩ ተግባራትን አስመልክቶ ከሚዲያዎች ጋር ቆይታ አድርገዋል ።
አቶ አንድነት አሸናፊ በመግለጫቸው፤በመጀመሪያዉ የፓርቲ ጉባዔ ዉሳኔ መነሻ እና ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ በክልሉ በተሰሩ ስራዎች የተሻለ ሰላምና ፀጥታ መረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በአንደኛው መደበኛ ጉባኤ ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች እና ካስተላለፋቸው በርካታ ውሳኔዎች መካከል አንዱ በሀገሪቱ በሁሉም አከባቢዎች የህዝብ ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ አንዱ ጉዳይ አንደሆነም ተናግረዋል።
በጉባኤው ከተቀመጠው ውሳኔ መነሻ እንዲሁም ከክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ ከፌደራል እስከ በክልሉ እስከ ወረዳ ድረስ የፀጥታ መዋቅሮችን በማጠናከር ከአመራሮች፣ከሀገር ሽማግሌዎች ፤ከማህበረሰብ ክፍሎችና ከተለያዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር የጋራ ውይይት መድረክ በመፍጠር ሰላምና ፀጥታ በማረጋገጥ የህዝብ ደህንነት ለማስጠበቅ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስዋል።
በዚህም በተለይ ቤንች ሸኮ፣ሸካ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም በካፋና ኮንታ ከፊል ቆላማና አርብቶ አደር ማህበረሰብ በሚኖሩባቸው አከባቢዎች ሲነሱ የነበሩ የፀጥታ ስጋቶች ለመቅረፍ በተሰራው ስራ የተሻለ ሰላም መምጣቱን ነው የጠቆሙት።
ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ ከአመራሩ እና ከፀጥታ መዋቅሮች ብሎም ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እርቅ በመፈጠር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ጫካ የገቡ ቡድኖችና ግለሰቦችን ትጥቅ በማስፈታት ከህዝቦች ጋር በማቀላቀል ጥያቄያቸውን በውይይት በመፍታት እና ህግ የማስከበር ስራዎች ተሰርቷል።
በዚህም በምዕራብ ኦሞ ዞን ቤሮ፣ጎርጌሻ እና ማጂ ወረዳዎች፤በቤንች ሸኮ ዞን ጉረፈርዳ እና ደቡብ ቤንች ወረዳዎች እንዲሁም በሸካ ዞን የኪ ወረዳና ቴፒ ከተማ የተቋረጠው መደበኛ መንግስታዊ እንቅስቃሴዎች ፣ ህዝብ ለህዝብ ግኝኑነት ፣የትራንስፖርት አገልግሎት እና በሰላም እጦት ምክንያት የቆሙ የልማት ስራዎች መጀመራቸውና በሰላም እጦት ሳቢያ ሲነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መቀረፋቸውን አቶ አንድነት አሸናፊ አንስተዋል።
ክልሉ ሰፋፊ ለግብርና እና እንቨስትመንት ስራዎች ትልቅ እምቅ አቅም ያለው አከባቢ በመሆኑ ቀደም ሲል በሰላም እጦት ምክንያት የልማት ስራዎችን ያቆሙ አርሶ አደሮችና በኢንቨስትመንት ተሰማርተው ተግባራቸውን ያቆሙ ባለሀብቶች ዳግም ወደ ተግባራቸው በመመመለሳቸው ለውጦች መጥቷል ነው ያሉት አቶ አንድነት አሸናፊ ።
የክልሉን ሰላም ለማድፍረስ ትጥቅ ታጥቀው ጫካ በመግባት ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አካላት በማጽዳት የእርስበርስ ግጭቶችን በባህላዊ መንገድ እርቅ የማውረድ ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመት ለብልፅግና ጉዞ ምቹ ምህዳር የሰላም መደላድል በመፈጠሩ በከተማም ሆነ በገጠር ሰፊ በግብርናም በአግልግሎት ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፍስት መጨመሩን ያነሱት አቶ አንድነት አሸናፊ በክልሉ በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካ የመጣው ምቹ እንቅስቃሴዎችን ለማጽናት በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።
ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰን በመሆኑ በተለያዩ ምክንያት ታጣቂዎች ከደቡብ ሱዳን ዘልቆ በመግባት በክልሉ ህዝብ ላይ የሚያደርሱትን ዘርፋ እና ሌሎች ጥቃቶችን የውስጥ አቅሞችን በማጠናከርና ከፌደራል ፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በ2017 ባለፉት ግማሽ ወራት የመከላከል ስራዎች በመስራት ዘራፊዎችን ከነትጥቃቸው በቁጥጥር ስራ የማዋልና የተዘረፉ ከብቶችን የማስመለስ ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል።
በድንበር አከባቢዎች የተጀመረው ፀጥታን የማስከበር ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል ከፌደራል ፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን ክልላዊ የውስጥ አቅሞችን በማጠናከር በድንበር አካባቢዎች ቋሚ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ችግሮችን ለማስቆም ቀጣይ ትኩረት የሚሰጥ ጉዳይ ይሆናል።
ከሁለተኛው ብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ በኋላ በድንበር እና በአርብቶ አደር አከባቢ ቀጠናዎች እና በውስጥም በአንዳንድ ቦታዎች ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች ላይ በትኩረት በመስራት መላው ክልሉን ከፀጥታ ስጋት ነፃ በማድረግ ወደ ልማት በመዞር ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል።
አቶ አንድነት አሸናፊ በማከልም የክልሉ መንግስትና መላው ሰላም ወዳድ ማህበረሰብ ክፍሎች ባለፉት ጊዜያት ለሰላም ለከፈለውን ቁርጠኝነት አመስግነው አሁንም ወጣቱ፣አመራሩ፣መላው ማህበረሰብ የተለመደውን ድጋፋቸውን አጠናክሮ በማስቀጠል ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
በፍቅር ከበደ
