
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፍትህ ቢሮ ተረቅቀው በህግ አውጪ አካላት የሚወጡ ህጎች ለክልሉ ህዝቦች ተደራሽ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መኾኑን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ በላይነህ አሪሞ ገለጹ።
ቢሮው ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር፤ ወጥነት ያለው ውጤታማና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት እየሰጠ ነው ያሉት ኃላፊው፣
የሕዝብንና የመንግስትን ጥቅም በተሟላ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ጠንካራ የሕግ ባለሙያዎችን በፍትህ ተቋማት በዕውቀትና በክህሎት ማብቃት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ በላይነህ አብራርተዋል።
በቢሮው ከሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አንዱ የህግ ማርቀቅ ስራ ነው ያሉት ኃላፊው፥ ክልሉ ከተመሠረበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ህጎችን በማውጣት፣ ፋይዳቸውን በመገምገም እና ከፌዴራል ህገ መንግስትና ሌሎች ህጎች ጋር በማጣጣም እየተሰራ ነው ብለዋል።
ክልሉ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስተው እስካሁን 48 አዋጆች ጸድቀዉ በሥራ ላይ መዋላቸውን የጠቆሙት አቶ በላይነህ የክልሉ የቤተሰብ ህግ የማርቀቅ ሥራ በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ 51 ደንቦች ተረቅቀውና በመስተዳደር ምክር ቤት ፀድቀው ተደራሽ በመሆን እየተሠራበት ያለ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚሁ በተጨማሪ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ህግ መጽደቅን ተከትሎ አስፈጻሚ ተቋማት ከህግ አረቃቀቅ አኳያ አስተያየት እንዲሰጥበትና እንዲመዘገብላቸዉ የላኳቸዉን 54 መመሪያዎችን የመመዝገብ ሥራም መሰራቱን ነው ያብራሩት።
በክልሉ የፀደቁ ህጎች ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት እና ከክልሉ ህገመንግስት መርሆች እና በህገ መንግስቱ ላይ የተደነገጉ መሠረታዊ መብቶችን እና ነጻነቶችን ባከበረ መልኩ እንድረቀቁ ለተቋማት ግንዛቤ ተሰጥቶ በክልሉ የሚወጡ ማናቸዉም ህጎች ከህገ-መንግስቱ ጋር እንዲጣጣሙ መደረጉንም ነው አቶ በላይነህ የገለጹት።
የሚወጡ አዋጆች ከህገ-መንግስቱ ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ አዋጅን ተከትሎ የሚወጡ ደንቦች የአስፈጻሚን ሥልጣን እና ተግባር ለማሻሻል እንደገና የወጣውን አዋጅ እና ሌሎችን ህጎችን የማይቃረኑ መሆናቸዉን የገለጹት ኃላፊ፣
በአስተዳደር ተቋማት የሚወጣ መመሪያም አዋጆችንና አዋጆችን ተከትሎ የወጡ ደንቦችን የማይቃረኑ እንዲሆኑ ተደርገው እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ የሚጸድቁ ህጎች የተዋረድ ደረጃቸዉን ጠብቀዉና የተጣጣሙ እንዲሆኑ በረቂቅ ዝግጅት ወቅት ትኩረት ተሰጥተው ተከናዉነዋል ብለዋል ኃላፊው።
በክልሉ የወጡ ህጎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የክልሉን ህዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መኾኑን ነው አቶ በላይነህ የጠቆሙት
በህግ አዉጪዉ፣ በህግ አስፈጻሚዉ እና በዳኝነት አካል መካካል የስልጣን ክፍፍል እና ገደብ እንዲኖር ተደርጎ እየተሰራ ያለ ሲሆን ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችም ልዩ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ትኩረት የተሰጠው እንደሆነም ተናግረዋል።
በክልሉ ፍትሐዊ የሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲፈጠርና እንዲጠናከር ግልጽ የሆነ የህግ ማዕቀፍ መዘርጋቱን የገለጹት አቶ በላይነህ፣ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች በተሻለ አደረጃጀት እና አሰራር በልማት ዕድገት ላይ የሚዉልበት ሥርዓት ተበጅቶለታል ብለዋል።
በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎች አግልግሎት ሰጪ ተቋማት በኩል የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶላቸዉ በክልሉ የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ ከአጠቃላይ ፀጥታ አኳያ የፍትህ እና የፀጥታ ተቋማት የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶላቸዉ በተናጥል እና በቅንጅት አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግስት የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት እንቅስቃሴዎችን እና ጠንካራ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት በመዘርጋት መንግስታዊ ሥራዎችን እንዲያከናዉንም በዘርፉ የወጡ ህጎች ማስቻላቸውንም ጠቁመዋል።
በመጨረሻም የወጡ ህጎች ለሰፊው የክልሉ ህዝቦች ከሚያስገኙት ጠቀሜታ አኳያ የአስፈጻሚ ተቋማት ከአስተዳደር ስነስርዓት ህግ መሠረታዊ መርህ ጋር በተጣጣመ መልኩ መመሪያ እንዲያወጡ እና አስተዳደራዊ ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው ተረድተው ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
በ2018 ዓ.ም የሚካሔደው 7ኛ ሀገራዊ ምርጫ ሠላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የምርጫ ተዋናይ የሆኑ በሙሉ የምርጫ ህግንና የህግ የበላይነትን ብቻ አክብረው እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
