




ቦንጋ የትምህርት ኮሌጅ ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ “በጥናት የተደገፈ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ” በሚል ጭብጥ እያካሄደ ነው።
በጉባኤው በተለያዩ ትምህርት እና ማህበረሰብ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ 30 የምርምር ውጤቶች እንደሚቀርቡ ማወቅ ተችሏል።
ጉባኤውን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያስጀመሩት የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ዱባሌ ሳህሌ:-የጋራ ጥረታችንን ወደፊት የሚያሻግረውን የኢኖቬሽን፣ የትብብርና ትስስር ጉባኤ በማዘጋጀታችን በኮሌጁ ማህበረሰብ ስም ኩራት ይሰማኛል ብለው እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተጣለብን ኃላፊነት እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።
በትምህርት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንደተመሠረት ተቋም፣ በምርምር የተደገፈ አበርክቶ እያደረገ እዚህ መድረሱን ያወሱት ዶ/ር ዱባሌ አሁን ላይ እንደ ሀገር እየታየ ያለውን የትምህርት ዘርፍ ፈተና ለማቅለል መሰል ምርምርና የውጤት ኮንፈረንስ የማዘጋጀት ጠቀሜታ ጉልህ መሆኑን አውስተዋል።
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ ዶ/ር ደስታ ገነመ:- እንደ ክልላችን የትምህርት ጥራት ስብራትና የተማሪዎች ተሳትፎ ላይ በትኩረት እየተሰራን መሆኑን ጠቅሰዋል።
የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ኮሌጁ የሚያከናነው ምርምር ውጤት ግብዓታችን ነው ብለዋል።
ዶ/ር ደስታ አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት አተገባበር ዙሪያም በጥናት የተደገፈ ግብረ መልስ ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል።
መሬት ላይ ወርዶ ለሀገሪቱ ፖሊሲ ግብዓት መሆን የሚችል ጥናትና ምርምር ሊካኸድ ይገባልም ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች የተገኙ ሲሆን ጭብጡን የሚዳስስ ቁልፍ ነጥቦች የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ በሆኑት ዶ/ር በቃሉ ፈረደ እየቀረበ ይገኛል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
