1. ሰላምን በተመለከተ
– ሰላም ሁሌም በውድ ዋጋ የሚገኝ ነው ፡፡በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 50 ዓመታት ሃሳብን አደራጅቶ የፖለቲካ ፍላጎትን ከማሳካት ይልቅ ጠመንጃን አማራጭ የማድረጉ ልምምድ ለሰላም እንቅፋት ፈጥሯል፤ወንድም ወንድሙን ገድሎ ምን አሳካ ብለን ብንጠይቅ መልሱ ምንም የሚለው ይሆናል፡፡ ችግሮች የሚፈቱትም በውይይት ብቻ ነው፡፡
2. ሸኔን በተመለከተ
– ጠመንጃ ታጥቆ የራስን ህዝብ እያሰቃዩ እታገልልሃለሁ ማለት ትርጉም የሌለው አካሄድ ነው፡፡ ሸኔ በኦሮሚያ ክልል እያደረገ ያለውም ይህንኑ ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም፣ በዴሞክራሲና በምርጫ ካልሆነ ጠመንጃ ይዞ ወደ ስልጣን መምጣት ፈጽሞ አይቻልም፡፡
3. በአማራ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ
– በአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች ባደረግነው ውይይት ከህዝቡ ሶስት ዋና ጥያቄዎች ተነስተውልናል፡፡ እነርሱም የልማት፣ የህገ መንግስት ማሻሻልና የወሰን ጥያቄዎች ናቸው፡፡ መንግስት በአማራ ክልል የሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ብዙ ርቀት ሄዷል፤ ለአብነትም 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አውጥተን በአባይ ወንዝ ላይ በአይነቱ ልዩ የሆነ ድልድይ ገንብተናል፡፡ በጎርጎራ ፕሮጀክት አማካኝነትም የክልሉን ቱሪዝም የሚያነቃቃ ስራ ተከናውኗል፡፡ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኩል ሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የሚሰራ ይሆናል፡፡
4. በአማራ ክልል የሚነሳውን የወሰን ጥያቄን በተመለከተ
– መንግስት ከአስተዳደር ወሰን ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች በውይይትና ዘላቂ ሰላም በሚያመጣ አግባብ እንዲፈታ በጽኑ ይፈልጋል፡፡ከግጭት የምናተርፈው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁንም ያለንን እናጎድላለን፡፡ በመሆኑም ሰላማዊ ንግግርና ውይይትን በማስቀደም የትኛውንም ጥያቄ መፍታት እንችላለን፡፡
5. የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸምን በተመለከተ
– ከስምምነቱ በኋላ የፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትብብር በርካታ ድሎችን አስመዝግበዋል፡፡ አውሮፕላን ማሪፊያዎችን በመጠገን የአየር ትራንስፖርት ማስጀመር ተችሏል፣ በ100 ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር በማውጣት የቴሌኮም አገልግሎት እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ ብሄራዊ ባንክ 10 ቢሊዮን ጥሬ ብር በመስጠት በክልሉ የባንክ አገልግሎት አስጀምሯል፡፡ በተጨማሪም ከስምምነቱ በኋላም 217 ፋብሪካዎች ስራ ጀምረዋል፡፡ የትምህርትና የጤና ተቋማትም አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ ይሄ ትልቅ እምርታ ነው፤ ነገር ግን በቀጣይም ቀሪ ስራዎች አሉ እነርሱን በትብብርና በውይይት መስራት ይገባል፡፡
6. ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት የሚከናወኑ ስራዎችን በተመለከተ
– መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት በዋናነት ሶስት ስራዎችን ያከናውናል፡፡ የመጀመሪያው ህግ ማስከበር ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በተጨማሪ በእያንዳንዷ ሰከንድ ለውይይት ዝግጁ የሆነ አካል ካለ ደግሞ በራችን ሀሌም ክፍት ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የስራ እድል ፈጠራን በማጠናከር ወጣቶችን ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር የሚከናወን ይሆናል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የማንግባባቸው ዋና ዋና ጉዳዮችን በአካታች አገራዊ ምክክር ለመፍታት ይሰራል፡፡
7. ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አተገባበርን በተመለከተ
– በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ ተምረው ሰልጥነው ተለቀዋል፡፡ ነገር ግን በሂደቱ የሚፈጠሩ ስህተቶች እንዳይኖሩ የአዋጁ መርማሪ ቦርድ እየሰራ ነው፡፡ ይህን አልፎ የሚከሰት ስህተት ካለም የማስተካከል ስራ የሚከናወን ይሆናል፡፡ የአዋጁ ዋነኛ ዓላማም የአገር ሰላምና ህልውናን መጠበቅ ነው፡፡
8. ብሔራዊ ትርክትን በተመለከተ
– በትናንት ስንባላ ነገን እንዳናፈርስ መጠንቀቅ አለብን፡፡ ነገን ለመዋጀት ትናንትን በእውቀት ማለፍ አለብን፡፡ ሁላችንም ለተፈጠሩ ችግሮች እውቅና ሰጥተን ለመፍትሄው በጋራ ለመስራት መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ትናንት የተፈጸሙ በደሎችን በይቅርታ ማለፍ አለብን፤ ይህም በጋራ ጠንካራ አገር ለመመስረት መሰረት ይሚጥል ነው፡፡ የርዋንዳ፣ ጀርመን፣ የደቡብ አፍሪካ ታሪክ የሚያስተምርን ይህን ነው፡፡
9. ድርቅን በተመለከተ
– ድርቅ በተለያዩ አከባቢዎች ተከስቷል፡፡ ድርቁ የሰው ህይወት እንዳይቀጥፍ ተባብረን መስራት አለብን፡፡ ነገር ግን ድርቁን ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል የሚደረገው ጥረት ተገቢነት የለውም፡፡ ድርቁን ለመከላከል በሚደረገው ስራ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው መንግስት ነው፡፡ መንግስት ድርቁን ለመከላከል ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በቀጣይም ፕሮጀክቶችን በማጠፈም ጭምር ድርቁ በዜጎች ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የሚሰራ ይሆናል፡፡
