መንግስት በሀገሪቱ ችግር እየፈጠሩ የሚገኙ አካላት ላይ ህግ ማስከበሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያካሄደ በሚገኘው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተነዛ ያለው የተዛባ መረጃና ፕሮፓጋንዳ አፍራሽ ነገሮችን እያባባሰ መሆኑን ተናግረዋል።
በአስተሳሰብ ረገድ ክላሽ ይዞ ዘራፍ የሚል የአርበኝነት አካሄድ አጥፊ መሆኑን ጠቅሰው የሰላምና የልማት አርበኝነትን በማጎልበት ለሀገርና ህዝብ ዘላቂ ሰላምና ልማት መስራት ይገባል ብለዋል።
ህዝብን በሚጎዳና ሀገርን ችግር ላይ የሚጥል የትጥቅ ትግል እንደማያዋጣና መንግስትም ሰላምን ለማፅናት ቀጣይነት ያለው እርምጃዎችን ይወስዳል ነው ያሉት።
መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃውን እንዲተው እጃችሁን አጣጥፋችሁ ተቀመጡ የሚሉን ኃይሎችም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል።
ህግ ለማስከበር ከሚወሰደው እርምጃ ጎን ለጎን ለሰላም ዝግጁ ለሆኑ አካላት ግን መንግስት ምንጊዜም ለውይይት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሀገራዊ ምክክር እየተፈቱ እንዲሄዱ ያደርጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መንገድ ሰላም ለማረጋገጥ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
