ከሸማቂ ሃይሎች ጋር ውይይት አድርጎ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሞከር አዲስ ነገር ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሀገራት የሚተገበር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም በዚሁ አግባብ ከሸኔ ጋር ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ መንግስት ባቀረበው የሰላም ጥሪ ሁሉም ሃይሎች በሰላም ወደሃገር ቤት ገብተው በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ትግላቸውን እንዲያካሂዱ ጥሪ ተደርጓል ብለዋል።
በዚሁ መሰረት ኦነግም፣ ኦብነግም፣ ግንቦት ሰባትም፣ ኢሕአፓም ሌሎችም ፓርቲዎች የተደረገላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሃገር ቤት ገብተው በተለያየ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ሁኔታ ከኦነግ ጋር የተደረገው ስምምነት ምን ነበረ ብሎ መጠይቅ ፋይዳ የለውም ሲሉ ገልጸዋል።
ኦነግን ወክለው በአመራር ደረጃ አስመራ ላይ ድርድር ያደረጉ ሰዎች አብዛኛዎቹ አዲስ አበባ መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከፊሉም የመንግስት ሃላፊነት ወስደው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
“የተለየ የሰላም ውይይት ካለ ግማሹ እዚህ ገብተው የሚሰሩበት ከፊሎቹ ደግሞ ጫካ ገብተው ሰው የሚያሰቃዩበት ምንም ምክንያት አይኖርም ሃሳቡ ለሁሉም አንድ ነው” ብለዋል።
በታንዛኒያ በነበረው የሰላም ውይይት የግልጸኝነት ችግር አለ ብለው ለሚያነሱ ሃይሎች ውይይት እንደሚካሄድ መንግስት ቀድሞ ማሳወቁን ጠቅሰዋል፡፡
በሰላም ንግግሩ የተጨመቀ ፍሬ ሃሳብ ሲኖር ለህዝብ ለመንገር መታቀዱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።
