ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ለኮንታ ብሔር የዘመን መለወጫ (ህንግጫ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)፣ የኮንታ ብሔር የዘመን መለወጫ የሆነውን (ህንግጫ) በዓልን ምክንያት በማድረግ ለመላው የብሔሩ ተወላጆች እና ወዳጆች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው፣ የህንግጫ በዓል የኮንታ ብሔር ጥንታዊ ባህል፣ እሴትና ማንነት የሚንጸባረቅበት ታላቅ የባህል ድግስ መሆኑን ገልጸዋል። “ይህ በዓል አሮጌውን ዓመት በይቅርታና በመተሳሰብ በመሸኘት፣ አዲሱን ዓመት በተስፋና በታደሰ መንፈስ የምንቀበልበት፤ ቂምና ቁርሾን አስወግደን ለአንድነትና ለወንድማማችነት እጆቻችንን የምንዘረጋበት የተቀደሰ ዕለት ነው” ሲሉ ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ተናግረዋል።
በበዓሉ ላይ የሚከናወኑት እንደ ሽምግልና፣ እርቅና እንደማዕድ ማጋራት ያሉ ማህበራዊ ክዋኔዎች የብሔሩ ህዝብ ለሰላማዊ አብሮ መኖር የሰጠውን ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያሳዩ ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው አመልክተዋል። እነዚህ በህንግጫ በዓል ውስጥ የታቀፉ መልካም እሴቶች፣ በክልሉና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚፈለገው ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም አስምረውበታል።
በመሆኑም መላው የኮንታ ብሔር ተወላጆች በዓሉን ሲያከብሩ የይቅርታ፣ የአንድነትና የመተሳሰብ እሴቶችን በማሰብና በመተግበር፣ አዲሱን ዘመን ለበለጠ ልማትና ለጋራ ብልጽግና በጋራ የሚሰራበት እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ይህን ታላቅ ባህልና እሴት ከሽማግሌዎች ተረክቦ ለቀጣይ ትውልድ እንዲያሻግር የድርሻውን እንዲወጣም አደራ ብለዋል።
በመጨረሻም ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤናና የብልጽግና እንዲሆን ያላቸውን ልባዊ ምኞት ገልጸው፣ ለመላው የብሔሩ ተወላጆች “መልካም የህንግጫ በዓል” እንዲሆን ተመኝተዋል።
በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መረጃዎችን ይከታተላሉን ![]()
በፌስቡክ https://www.facebook.com/sowestcommunication/
በድረገጽ www.southwestcomunications.gov.et
በኢንስታግራም https://instagram.com/southwest_communications
በትዊተር twitter.com/sweprs
በቲክቶክ https://www.tiktok.com/@southwest.communi
በቴሌግራም https://t.me/Debubmierab
በዩቲዩብ youtube.com/@southwestgovcommunication
በዋትስአፕ
https://whatsapp.com/channel/0029VbAiSCpGE56ue7VyJJ3x
https://www.linkedin4v .com/company/southwest-communications/
