የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

Spread the love

ሪፖርታዥ


ያደጉ ሀገራት ለትምህርት ከፍተኛ የሆነ በጀት በመበጀት በቴክኖሎጂ የዳበሩ ዜጋ እና ተማሪዎች እንዲፈጠሩ በከፍተኛ መንገድ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህንኑ ዘርፍ ለመለዋጥ የት/ቤቶች መሠረተ ልማት የማሻሻል ሃገራዊ ንቅናቄ በመጀመር ሁሉም ት/ቤት መደገፍ እንዳለበት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ።

እንደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት መስፈርትን የማያሟሉ በመሆናቸው ይህም የትምህርት ጥራት አንዱ ችግር ሆኗል፡፡ የ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ንቅናቄ በየደረጃው ከክልል ጀምሮ በተዋረድ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ እየተደረገ ይገኛል::

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ና የመማር ማስተመር ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ደስታ ገነመ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ በርካታ ርቀቶችን የተጓዝን ቢሆንም ጥራት ያለው ትምህርት ከመስጠት አንፃር በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት ገልፀው ለዚህም የትምህርት ቤት መሠረተ ልማት መሻሻል ለትምህርት ጥራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ያለውን የትምህርት ቤቶችን ነባራዊ ሁኔታ መቀየር ካልቻልን በአለም ተወዳዳሪ ትውልድ መፍጠር አንችልም ያሉት ኃላፊው ይህንን ችግር በመንግስት አቅም ብቻ መፍታት ስለማይቻል ለዚህም ህዝባዊ ንቅናቄ መጀመሩን ተናግረዋል።

በክልሉ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራ ውብና ምቹ ለማድረግ “ትምህርት ለትውልድ“ በሚል በተካሄደው ህዝባዊ ንቅናቄን እስከአሁን ከ261 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

ቢሮው በህብረተሰብ ተሳትፎ በዓመቱ ከማህበረሰቡ የገንዘብ ፣ ቁሳቁስ ፣ ጉልበትና ክህሎት አስተዋጽኦ 283 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ በስድስት ወራት የዕቅዱን 92.23 በመቶ ማሳካት መቻሉንም ዶክተር ደስታ ገነሜ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በግማሽ ዓመቱ ለትምህርት ስራው የተጠቀሰውን ያህል ሀብት ማሰባሰብ የተቻለው ማህበረሰቡ ለትምህርት ስራ በሰጠው ትኩረት ፣ የትምህርትን መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ በመገባቱና የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ አጀንዳ ተደርጎ በመሰራቱ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ባሉት ከደረጃ በታች የሆኑ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 158 የመማያ ክፍሎችን ጥገና በማድረግ ወደ ተሻለ ደረጃ የማምጣት ፣ በቅድመ አንደኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 488 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ በማከናወን፤ መሰረተ ልማት የማሻሻል እና የማስፋፋት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪም 18 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ጥገና እና 65 አዳዲስ የመመሪያ ክፍሎችን፣ 8 የቤተመጻሕፍትና ግንባታ በማከናወን፣ የማሻሻል፣ የማስፋፋት እንዲሁም 50 የመምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ከእነዚህም ወስጥ አንዳንዶቹ ትምህርት ቤቶች ጥገና እና ግንባታ ስራ ተጠናቆ ርክብክብ እየተፈጸመ መሆኑን ዶክተር ደስታ አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ለ2016 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ውጤታማነት የመማሪያ ክፍሎች፣ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ግንባታና የተለያዩ ሥልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውም ተገልጿል።

በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ664 ሺህ 640 በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው በትምህርት ገበታ ላይ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡

የሰለጠነ የሰው ሀይል ሊኖር የሚችለው በትምህርት ስለሆነ ለትምህርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የተጀመረ ቢሆንም አሁንም የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ማሻሻል ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የትምህርት ዘርፉን በማጠናከርና ቁሳቁስ የማሟላት ሥራ በመስራትና ትምህርት ቤቶችን ለተማሪዎች ምቹ እና ሳቢ በማድረግ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ትልቅ ሚና ስላለው ለትዉልድ ግንባታ ሥራ ሁሉም በጋራ መረባረብ እንደሚገባም ዶ/ር ደስታ ጠይቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *