




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከፌደራል ግብርና ሚንስትር ጋር በመተባበር በክልሉ በስራ ላይ ከሚገኙ የግብርና ኢንቨስትመንት ባለሀብቶችና ባለድርሻ ጋር የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካኸደ ነው።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትልና የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ አቀርቦት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስራት አሰፋ: መንግስት ላለፉት የለውጥ ዓመታት የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ ለማዘመን አዲስ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ አጽድቀው ወደ ትግበራ መግባቱን ጠቅሰዋል።
ግብርና ለሀገራችን ብልጽግና ጉዞ እውን መሆን የሚወስደው ድርሻ የጎላ መሆኑን ያወሱት አቶ አስራት: በኤክስፖርት ምንጭነት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በምግብ ዋስትና እንዲሁም በአጠቃላይ የሀገሪቱን ዕድገት በእጅጉ የሚያግዝ ዘርፍ መሆኑን አንስተዋል።
መንግስት የግብርና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የግብርና ምርት ቴክኖሎጂ እያስፋፋ ነው ያሉት አቶ አስራት በክልላችንም ከለውጡ በፊት 140 የነበረውን የእርሻ ኢንቨስትመንት ወደ 544 በማድረስ 177 ሺህ ሔክታር ላይ እንዲያለሙ ተደርጓል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ለእርሻ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ብዙ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቁመው መሬት ወስደው ያላለሙት በሙሉ አቅም ወደ ምርት እንዲገቡ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር የማቀናጀትና ኮንትራት እርሻን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መሰራቱንም ገልጸዋል።
ባለሀብቱን ከአርሶ አደሩ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ተደርገው አርሶ አደሩ የመሬት አጠቃቀም አቅሙን ከፍ አድርገው የግብዓትና ቴክኖሎጂ እንዲጠሙ መደረጉን ተናግረዋል።
በኢፌዴሪ ግብርና ሚንስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ አበበ በበኩላቸው ግብርና ዘርፍ የማክሮ ኢኮኖሚን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ዕድገት አይተኬ ሚና የሚጫወትና ከ50 በመቶ በላይ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ነው ብለዋል።
አዲሱ የግብርና ፖሊሲ 10 የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ልዩ አጽንኦት መስጠቱን ጠቁመው የእርሻ ኢንቨስትመንትና ግብይት ትግበራ ከዋነኞቹ በማድረግ የሜካናይዜሽን ስራን ለማሳለጥ ከ550 በላይ የቴክኖሎጂ ዕቃዎች ከቀረጥ ነጻ ሆኖ እንዲገቡ መደረጉን ገልጠዋል።
የኮንትራንት እርሻ አዋጅ በፓርላማ ጸድቆ አርሶ አደሩንና ባለ ሀብቱን በጋራ እንዲጠቀሙ ማስቻሉን ጠቅሰው መድረኩም የግሉን ዘርፍ ለማጠናከር ሁለት ግዙፍ ኢንቨስትመንት ኩባንያዎች በክልሉ ከተሰማሩት አልሚዎች ጋር በኮንትራት እርሻ ተባብረው እንዲሰሩ ማድረግ ነው ብለዋል።
በመድረኩ የፌደራልና የክልል መንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ኢንቨስተሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን የክልሉ እርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ሰነድ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ከበደ ተስፋዬ እያቀረቡ ይገኛሉ።
በአሻግሬ ገ/ ወልድ
