




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በንቅናቄ መድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት ትውልድ የሚያስቀጥሉና አገር የሚያሻግሩ እናቶችንና ሴቶችን የሚያጠቃውን የማህፀን በር ካንሰር በሽታን በቅድመ ምርመራና በክትባት ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈጋል ብለዋል።
አቶ ኢብራሂም አክለውም በክልሉ በበጀት አመቱ ባለፉት ስምንት ወራት ምርመራ ከተደረጉ 8021 እናቶች 272 እናቶች ላይ የቅድመ ካንሰር ምልክት መታየቱንም አንስተዋል።
ይሄ አሀዝ ቀላል የማይባል በመሆኑ እናቶች የካንሰር ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉና ልጃገረዶች ክትባት እንዲወስዱ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የቢሮው ምክትል ሀላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሀይሌ ዘውዴ በበኩላቸው በክልሉ የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ውጤታማና ስኬታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
በክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክተር አቶ መሠረት ወ/ማሪያም በበኩላቸው የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እንደ አገር ከተጀመረ ወደ ስምንት አመት መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም ውጤት እየተገኘ ቢመጣም የሚፈለገውን ውጤት በማምጣት የሴቶችን ጤና ለመጠበቅ በሚሰጠው በዚሁ የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት በተለይ እድሜአቸው ከዘጠኝ አመት በላይ የሆኑ ልጃገረዶች እንዲከተቡ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በመድረኩ የክልልና የዞና ጤና ዘርፍ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።
