




ጉባኤውን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ዮሐንስ ካሳሁን ምክር ቤቱ በሕገ-መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሰላም ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዞኑ አሁን ላይ ለሚገኝበት ዘላቂ ሠላም ምክር ቤቱ ጉልህ ሚና መጫወቱን ጠቅሰው ይህንንም አጽንቶ ለማስቀጠል ሁሉም የድርሻውን የመወጣት ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።
የዘንድሮው ጉባኤ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሚካሄድበት ዋዜማ ላይ መሆኑን ልዩ እንደሚያደርገው የገለጹት ዋና አፈ ጉባኤው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የወጡ ሕጎችና ደንቦች በተግባር ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወኑ የሥራ አፈጻጸሞች ውጤቶች የታዩ ቢሆንም በጉባኤው ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ መሠረታዊ ችግሮች መኖራቸውን አቶ ዮሐንስ ጠቁመዋል።
በተለይም በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ዘንድ የሚስተዋሉ ክፍተቶች መፈታት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚታዩትን እንደ ሕገ-ወጥ የታሪፍ ጭማሪ፣ ትርፍ መጫንና ከስምሪት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ግድፈቶች ሕዝቡን ለእንግልት እየዳረጉ መሆኑን የገለጹት ዋና አፈ ጉባኤው ተቋማቱ ራሳቸውን ሊፈትሹና ጠንካራ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም በግብርናው ዘርፍ የቡና ጥራትን ማስጠበቅ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በገቢ አሰባሰብና በጤናው ዘርፍ ውጤታማ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ በአፅንኦት አንስተዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ አበበ ማሞ የዞኑን አስፈጻሚ አካላት የ2018 ዓ.ም የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ይገኛል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
