




የክልሉ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ የ3ኛ ዓመት 5ኛ መደበኛ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ እና 3ኛ ዓመት 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ መርምሮ በማፅደቅ እንዲሁም የ2018 ግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በመገምገም ተጠናቀቀ።
በግማሽ ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራትን የተመለከተ የፎቶ አዉደ ራዕይ መርሐ ግብርም ተከናውኗል።
የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት በ2018 በጀት ዓመት ሀገራዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረጉ 5 ግቦች ያሉትን ዕቅድ በምክር ቤቱ በማጸደቅ ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን የመፈጸም አቅሙም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱም ተጠቁሟል።
ለአብነትም 20ኛው የህዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በተለየ መልኩ እንዲከበር መደረጉን፣የብሔረሰቦች የጋራ እሴቶችን ለመገንባት በዕቅድ የተያዘውን ለማሳካት ለህትመት ዝግጁ መደረጉ፣ሚዲያን በመጠቀም በየብሔረሰቦች ቋንቋዎች እና በአማርኛ ቋንቋ የህገመንግስት እና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ላይ ግንዛቤ መፈጠሩን፣የሚከሰቱ እና ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶች እና አለመግባባቶችን በራስ አቅም ለመፍታት የሚያስችል ክልላዊ የግጭት አፈታት እና የሠላም ግንባታ ስትራቴጂ ሰነድ መዘጋጀቱም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በቀረበው የ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት መነሻ በማድረግ በምክር ቤቱ አባላት ሀሳብ እና አስተያየት ተሰጥቷል።
በዋናነትም የግጭት መንስዔ የሆኑ የተፈጥሮ አጠቃቀም ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ፣የክልሉ ገፅታ ግንባታ ላይ መስራት፣በወሰን ይገባኛል ለሚከሰቱ ግጭቶች መፍትሔ ማበጀት፣የውስጥ ሠላምን ለማስፈን በሚፈለገው ፍጥነት መሄድ እንደሚያስፈልግ፣የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ተሳትፎ ማሳደግ፣የ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቅንጅት መስራት፣ የህዝቦች የዘመናት ትስስር እና አንድነት ማጠናከር እና መሰል ተግባራትን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል የሚሉ ነጥቦች ላይ በቀጣይ በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባ በምክር ቤቱ አባላት ሀሳብ እና አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማዉ ዘዉዴ የክልሉ መንግስት የክልሉን ህዝቦች አንድነትና ትብብር የሚያጠናክሩ፣የተገኘዉን ሠላም የሚያጸኑ እና በየአካባቢዉ ያሉ የመልካም አሰተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት መጠነ ሰፊ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዉ ቀሪ ተግባራት ላይ የምክር ቤት አባላቱ ሚናቸዉን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።
የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና ምክትል አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ መሠለ ከበደ እንደተናገሩት በክልሉ የሚገኙ ብሔረሰቦችን አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ እሴቶችን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት የሁሉም አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ጌታቸው ኬኒ ምክር ቤቱ ከሌሎች ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ፈጥሮ የሚነሱ የወሰን ይገባኛልና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሰራ በመሆኑ በዘርፉም ዕቅድ የመፈጸም አቅሙም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
