‎‎ባለፉት ስምንት ወራት በተከናወኑ አጠቃላይ የጤና ተግባራት አበረታች ውጤቶች መዝገባቸዉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ በበጀት አመቱ ያለፉት የስምንት ወራት አጠቃላይ የጤና ተግባራት አፈፃፀም እየገመገመ ይገኛል።

በአፈፃፀም ግምገማ ላይ የተገኙ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በክልሉ ባለፉት ስምንት ወራት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ አጠቃላይ የጤና ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በእናቶችና ህፃናት ዘርፍ ከነፍስ ጡር እናቶች ማቆያ ማዕከልና ከህፃናት ክትባት ጋር በተያያዘ በሽፋን የተገኙ ውጤቶችን በጥራት መድገም እንደሚገባም አቶ ኢብራሂም አብራርተዋል።

ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር በተለይ የወባ በሽታ ለመከላከል ባለፉት ሁለት አመት በተከናወኑ ጠንካራ ተግባራት መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት መቻሉ ተገልጧል።

በተገኘው ለውጥ መዘናጋት አያስፈልግም ያሉት አቶ ኢብራሂም በክልሉ የበልግ ዝናብ በጊዜ መጀመሩ ለወባ በሽታ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጠር የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባራት አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል።

ኤችአይቪ ኤይድስ በተመለከተ በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ የተገኘ እንደሆነ የተነገር ሲሆን በተለይ ተጋላጭ የሆኑ አከባቢዎችን በመለየት የሚደረግ የምርመራ ተግባር ትኩረት የሚሻ እንደሆነ አንስተዋል።

የፅዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭ አካል የሆነውን የፅዱ ጤና ተቋምና ሞዴል መንደር ለመፍጠር የተጀመሩ ተግባራት ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተጠይቋል።

በህክምና አገለግሎት ዘርፍ የመጡ ለውጦችን አጠናክሮ በማስቀጠል የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ በልዩ ትኩረት ሊሰራ ይገባል ተብሏል።

የጤና ባለሙያዎች ፍቃድ ጋር በተያያዘ የተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ቢሆኑም የመረጃ ትክክለኛነቱን ከማጥራት አንፃር በተገቢው ሊሰራ ይገባል።

በህብረተሰብ ጤና ዙሪያ የተጀመሩ የተሻሉ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን በምርመራ ዘርፍ ያሉ ተግባራትን ማሳደግ እንደሚገባ ተብራርቷል።

ከመረጃ ጥራትና ወቅታዊነት ጋር ያለው አፈፃፀም ከባለፉት ጊዜያት አንፃር መሻሻሎች ቢኖሩም በአንዳንድ ዞኖች ያለው ማነቆ ሊፈታ እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል።

በመድረኩ የስድስቱም ዞኖች የጤና መምሪያ ሀላፊዎች፣ የልማት ዕቅድ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *