የኮንታ ልማት ማህበር 10 ሺህ ቶን የድንጋይ ከሰል ምርት ለፋብሪካ ለማቅረብ እየሠራ እንደሚገኝ ተገለፀ።

Spread the love

በኮንታ ዞን ጪዳ ከተማ አስተዳደር የድንጋይ ከሰል ማምረት፣ የግብርናና ሌሎች ልማት ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ የዞኑ ከፍተኛ የመንግስትና የፓርቲ ሥራ ኃላፊዎች ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነጋ አበራ የተፈጥሮ ሀብትን ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ ሲናውል አካባቢን በሚጠብቅና የተሻለ ገቢ በሚያስገኝ መልኩ መሆን እንደሚገባ ጠቁመው በኮንታ ልማት ማህበር ባለቤትነት እየተካሄደ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል የማምረት ሂደት ጥሩ ጅማሮ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

የማዕድን ልማት ስራ የአካባቢ ደህንነትን በሚጠብቅ መልኩ መልማት እንደሚገባ የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ስራ መስክ የተሰማሩ አካላት ያሳዩትን ክፍተት በሚያርም መልኩ መምራት እንደሚያሻ በመግለፅ የምርት ሂደቱ ላይ ያለው መልካም ጅማሮ በግብይት ላይም ተጠናክሮ እንዲሰራ አስገንዝበዋል።

አክለውም በዞኑ ውስጥ በተመሳሳይ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በሙሉ አቅማቸው ወደስራ እንዲገቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በሀገር ደረጃ የሚታዩ የገበያ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው አንስተዋል።

የኮንታ ልማት ማህበር ቦርድ ሰብሳቢና የዞኑ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ታከለ ተስፉ በበኩላቸው ልማት ማህበሩ ብዙ ሀብቶችን መፍጠር በሚችሉ ልማት ዘርፎች ላይ መሳተፍ አንዱ አቅጣጫ ተደርጎ የተጀመረ በመሆኑ በአካባቢው በከፍተኛ ሁኔታ የሚገኘውን የድንጋይ ከሰል ማምረት ሥራ ላይ መሳተፍ አንደኛው ተግባር ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።

የድንጋይ ከሰል የማምረቱ ሥራ የመንገድ ከፈታና ፍቃድ የማውጣት ሥራ ከተሰራ በኋላ ወደ ምርት ማምረት ሥራ መገባቱን ያስረዱት አቶ ታከለ በቀጣይም የገበያ ትስስር የማጠናከርና የማህበሩን ኢኮኖሚ አቅምን ለማሣደግ ከፍተኛ ሀብት መፍጠር በሚያስችል ደረጃ እየተሠራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የልማት ማህበሩ ተወካይ አቶ ታረቀኝ መኩሪያ በበኩላቸው ልማት ማህበሩ ከመሬት ጥናት እስከ ምርት ማምረት ድረስ በአነስተኛ ወጪ ሥራዎችን በማከናወን ምርቱን ወደ ፋብሪካ መጫን ደረጃ በመድረስ እያመረቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለፋብሪካ 10 ሺህ ቶን ምርት ለማቅረብ ተዋውለው እስካሁን 180 ቶን የሚያክል ምርት ወደ ፋብሪካ መጫን መቻላቸውንም አክለዋል።

የድንጋይ ከሰል ማዕድን አለኝታ ቦታዎች ቅድመ ልየታ ባለፈ ተጨማሪ ጥናት በማድረግ በአከባቢ ተፈጥሮ ላይ ጉዳት በማያስከትል ሁኔታ ምርት እየተመረተ መሆኑም ተጠቁሟል።

በተያያዘም በጪዳ ከተማ አስተዳደር በሙሉ ፓኬጅ እየለማ የሚገኘውን 60 ሄክታር የበቆሎና 5 ሄክታር ቀይ ሽንኩርት ማሳዎች ጉብኝት የተደረገ ሲሆን በዞኑ በበልግ እርሻ እየለማ ያለው ስራ አበረታች መሆኑ ተገልጿል።

አመራሮቹ የድንጋይ ከሰል ማምረትና ግብርና ስራዎች በተጨማሪ ግንባታው የተቋረጠውን የጪዳ 2ኛ ደረጃ ት/ቤትና ሌሎች ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ተዘዋውረው መጎብኘታቸዉን የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *