





“ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ” በሚል መርህ ቃል ክልል ዓቀፍ የብክለት መግቻ ንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
በንቅናቄው ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶር) እንዳሉት፣የአረንጓዴ አሻራ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና የአካባቢ ብክለት መግቻ የንቅናቄ ተግባራትን ከዘመቻ ባለፈ ተቋማት የየራሳቸውን ዕቅድ ይዘው በተቀናጀ መልኩ መመራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የተጀመሩ የገጠርና የከተማ የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ የሌማት ትሩፋት ስራዎች፣ በፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቀ የታቀፉ ተግባራት እንዲሁም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን በክልሉ በሚገኙ በሁሉም ቀበሌዎች ውጤታማ ለማድረግ በተለየ መልኩ መምራት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የክልሉ የደን፣አካባቢ ጥበቃ እና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ኢንጂነር አስራት ገ/ማርያም የጽዱ ኢትዮጵያ የብክለት መግቻ ንቅናቄ ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት እንዳብራሩት ፣ ለሰው ህይወት ጠንቅ የሆኑ የኬሚካል ቆሻሻዎችን የሚያመጡ ተቋማት ላይ ክትትል በማድረግ ለመፍትሔው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በመድረኩ የኢፌደሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሚ ከተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች እና አስተያየት ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፣ የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ መሆኑን ጠቅሰው ጽዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ተሳታፊዎች ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ እንደሆነም ገልጸዋል።
በክልሉ የተጀመረውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ለመሆን የአንድ አቅመ ደካማ ቤት ለመስራት ቃል የገቡ ሲሆን ለጽዱ ኢትዮጵያ ስራ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
በመጨረሻም በክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስተባባሪነት ክርዕሰ መስተዳድሩ ለአካል ጉዳተኞች የዊልቼር ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዞኖች የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በቦንጋ ከተማ “ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድረግ ” በሚል መሪ ቃል ክልል አቀፍ የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ እና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መድረክ ላይ የክልል ከፍተኛ አመራሮች፤ የዞን፤ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች፤ የሀገር ሽማግሌዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
በካሳሁን አሰፋ
