ኢትዮጵያና ብራዚል በብሪክስ ማዕቀፍ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

Spread the love

ኢትዮጵያና ብራዚል በብሪክስ ማዕቀፍ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን እና አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ በብሪክስ የብራዚል ዋና አስተባባሪ (ሼርፓ) አምባሳደር ኤድዋርዶ ሳቦአ ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ልዑልሰገድ ከአስተባባሪው ጋር የ2025 የብሪክስ ፕሬዝዳንት በሆነችው ብራዚል የቅድሚያ ትኩረት በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው ኢትዮጵያ እና ብራዚል በብሪክስ ማዕቀፍ ያላቸውን ትብብር እና አጋርነት ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አመልክተዋል።

ብራዚል በብሪክስ ፕሬዝዳንትነቷ ወቅት “የአዳጊ ሃገራት ትብብርን በማጠናከር ይበልጥ አካታች እና ዘላቂ አስተዳደር መፍጠር” በሚል መሪ ሀሳብ የዓለም አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ እንዲደረግበት እና የአዳጊ ሃገራት ትብብር እንዲጎለብት በትኩረት እንደምትሰራ አመልክተዋል።

የብራዚል የቅድሚያ ትኩረቶች ከኢትዮጵያ የልማት እቅዶች እና ህልሞች ጋር የተጣጣሙ ናቸው ያሉት አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ብራዚል በብሪክስ ፕሬዝዳንትነቷ ወቅት ለምታከናውናቸው ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *