የ2017 የከተራ እና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

Spread the love

እንኳን ለ2017 ለከተራና ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን የገለፁት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰብስቤ ሻዎኖ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በአላት አንዱ የሆነዉ የከተራና የጥምቀት በዓላት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ ፖሊስ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በክልሉ በስድስቱም ዞኖች፣ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች 850 ታቦታት እንዳሉ መረጃዎች መሠብሰቡን ያመለከቱት ኮምሽነር ሰብስቤ እነዚህ ታቦቶች ወደ ተዘጋጀላቸዉ 612 ጥምቀተ ባህር ጊዜያዊ ማደሪያቸዉ ጥር 10 ቀን 2017 ዓ.ም በምዕመናን ታጅበዉ የሚያቀኑ በመሆኑ መደበኛ ፖሊስ፣ የክልሉ ፖሊስ ከአድማ ብተና፣ ከሚሊሻ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በቋሚና በተንቀሳቃሽ ጥበቃዎች እንደሚደረጉ አስረድተዋል።

በዓሉ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በአደባባይ የሚከበር በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የበዓሉ ታዳሚዎች ላይ የሞባይል፣የኪስ ቦርሳና ጌጣጌጦች የስርቆት ወንጀል እንዳያጋጥም በባህረ ጥምቀቱ አካባቢና አማካኝ ስፍራዎች ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያ ተከፍተው አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ መመቻቸቱን ጠቁመዋል።

በበዓሉ ላይ ግጭት ቀስቃሽ ፅሁፎችን፣ህትመት ዉጤት ትሸርቶችን እና የፖለቲካ ነክ መልዕክቶችን ይዞ መገኘትና ማሰራጨት እንደማይገባ የገለፁት ኮምሽነሩ ሰላም ወዳዱ ህዝብ እንደቀደመዉ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች የበዓሉን ሰላም የሚያውኩ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከትም በአካባቢው ላሉ የፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ኮምሽነር ሰብስቤ ለመላዉ የእምነቱ ተከታዮችና ለፖሊስ አመራሮችና አባላት እንኳን ለከተራ እና ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በዓሉ የሰላም፣የጤና እና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል ሲል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሮክቶሬት ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *