




በቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን የተመራ የዞን አመራሮች ቡድን በዞኑ እየተገነቡ ያሉ ካፒታል ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ በ2015 ዓመተ ምህረት የግንባታ ስራቸው የተጀመሩ የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የዞኑ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ የቢሮ ህንጻ ግንባታዎች ተጎብኝተዋል።
በግንባታዎች አፈፃፀምም የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህንጻ ፊዚካል 40 በመቶ እንዲሁም ፋይናንሻያል 27 በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን የዞኑ ግብርና መምሪያ ህንጻ ፊዚካል 52 በመቶ እንዲሁም ፋይናንሺያል 34 በመቶ መሆኑ በጥሩ አፈፃጸም ላይ የሚገኝ መሆኑ በምልከታ ወቅት ተገልጿል።
የቤንች ሸኮ የማህበረሰብ ቴሌቪዥን የስቱዲዮ ግንባታ ሂደቱም 90 በመቶ መድረሱ ተጠቁሟል። የዞን አስተዳደር ህንጻ የጥገና ስራ በቅርቡ የተጀመረ ሲሆን የግንባታ ሂደቱ በአመራሮቹ ተጎብኝቷል።
ሌላው በ2013 የግንባታ ሂደቱ የተጀመረው የሚዛን አማን ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ ለረጅም አመታት የተጓተተና ዛሬ ላይ የግንባታ ሂደቱ ያልተጠናቀቀ መሆኑ በደካማ አፈፃጸም ታይቷል። አሁን ላይ የግንባታ ሂደቱ 60 በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባም አቅጣጫ ተቀምጧል።
በመጨረሻም የጉብኝቱ አካል የሆነው በሚዛን ሁለገብ አዳራሽ የክብር እንግዶች ማረፊያ ህንጻ የግንባታ ሂደት ምልከታ የተደረገበት ሲሆን ግንባታው በደካማ አፈጻጸም የታየ ሆኗል።
በደካማ አፈፃጸም ውስጥ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ አቅጣጫ የተሰጠ ሲሆን ወደ ስራ በማይገቡት ላይ አሰራር ተጠብቆ እርምጃ እንደሚወሰድም በምልከታው ተገልጿል ሲል የቤንች ሸኮ ዞን የመንግሰት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።
